Search

አዲሱ የተስፋ ምዕራፍ

ዓርብ ኅዳር 26, 2018 233

ለረጅም ጊዜ ሰላም ሲፈልግ የነበረው የአማራ ክልል ሕዝብ በተለያዩ ጊዜያት ጥሪውን አቅርቧል፤ ለሰላሙ ይበጃል ያለውንም ሃሳብ ሲሰነዝር ቆይቷል።

ለዚህ ሰላም ፈላጊው ሕዝብ አዲስ የተስፋ ምዕራፍ የጀመረበት ታሪካዊ ክስተት ተስተናግዷል።

የጠመንጃ ድምፅ በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት፣ የኃይል አማራጭ በሰላም ስምምነት ተለውጦ፤ በክልሉ መንግስትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የዘላቂ ሰላም ስምምነት ፊርማ ተካሂዷል።

ይህንን ለክልሉ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያውያን እፎይታን እንደሚሰጥ የታመነበትን ስምምነት፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) ተወካይ ካፕቴን ማስረሻ ሰጤ ፈርመዋል።

የፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ በፊታቸው ላይ በሚነበበው ተስፋ ስምምነቱ ለክልሉ ሕዝብ የሰላም አየርን ይዞ እንደሚመጣ አበክረው ተናግረዋል።

ይህ ስምምነት ለአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ለመንግስትም፣ ለሕዝብም ሆነ ለታጣቂዎቹ የጋራ ድል እና እፎይታ የሚሰጥ መሆኑን ነው ያስረዱት።

የመንግሥት አቋም ግልጽ ነበር፤ ማንኛውም ጥያቄ አለን የሚሉ ወገኖች ካሉ፣ መፍትሔው ያለው በጥይት ሳይሆን፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ሃሳብ ነው። ይህ የመንግሥት የቁርጠኝነት በአማራ ክልል በተግባር ሲተረጎም ታይቷል። የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ክስተቱ ከፖለቲካዊ ስምምነት በላይ የላቀ ትርጉም አለው።

ሕዝቡ "እፎይ" ብሎ የሚተነፍስበት የዕረፍት ቀን ማብሰሪያም ሆኗል። ሰላም እንደ አየር ለሚያስፈልገው ለዚያ አካባቢ ሕዝብ፣ ውይይት እና ስምምነት የህልውና ጉዳይ ነው። ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን የሰላም አማራጭ "ብቸኛው መውጫ" ሲሉ ይገልጹታል።

እውነት ነው፤ ባለፉት ጊዜያት የነበረው ግጭት የሕዝብን አንጡራ ሀብት አውድሟል፤ ማኅበራዊ ትስስርን በጣጥሷል። ዛሬ የተጀመረው ጉዞ ግን ያንን የተሰበረ ልብ ለመጠገን እና የጠፋውን ሀብት ለማዳን የተደረገ ወሳኝ እርምጃ ተደርጎ ይወሰዳል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው መሃል አንድ እውነትን አነሱ፤ ይህ ስምምነት "ከግጭት በፊት መምጣት የነበረበት" እንደነበር አልሸሸጉም። ምክንያቱም ከግጭት የሚተርፍ የለም፤ በጦርነት ተጀምሮ በጦርነት የሚገኝ መብትም ሆነ ጥቅም እንደሌለ የቅርብ ጊዜው ታሪክ ምስክር ነው።

በሌላኛው የስምምነቱ ጠረጴዛው ጫፍ የነበሩት የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ተወካይ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤም፣ የሰላሙን አስፈላጊነት በምሬት እና በተስፋ ቅይጥ ስሜት ገለጡ።

እንደ ካፒቴኑ እምነት፤ የሕዝብን ጥያቄ አንግቦ መታገል አንድ ነገር ነው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ እንድትበታተን ከሚፈልጉ የባዕድ ኃይሎች እና ተገንጣዮች ጋር ማበር የሕዝብን ጥያቄ መካድ እንጂ መታገል አይደለም።

"አጥፊነት" ሲሉ የጠሩት ይህ አካሄድ፣ ሊገታ እንደሚገባውም አነሱ።

የጠመንጃው ድምፅ መገታት ለአማራ ሕዝብ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጥያቄ መሆኑንም ነው ያስረዱት።

ይህ አዲስ የተስፋ ምዕራፍ ዓለም አቀፍ ድጋፍንም የሚሻ ነው። የተጀመረው የሰላም ጉዞ ፍሬ አፍርቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ዓለም አቀፍ ተቋማት እጃቸውን እንዲዘረጉ ጥሪ ቀርቧል።

የጦርነቱን አዙሪት ለመግታት በጀርባ ሆነው ሲደክሙ ለነበሩ ሁሉ ምስጋና ቀርቦላቸዋል።

ኢጋድም ይህንን ጅምር በሩቁ አልተመለከተም፤ "እንኳን ደስ አላችሁ" ሲል መልካም ምኞቱን የገለጸ ሲሆን፣ አሁንም በጫካ የቀሩና ጣታቸው ከአፈሙዝ ጋር ያዋደዱ ሌሎች ኃይሎች፣ ይህንን ታሪካዊ የሰላም ባቡር እንዲቀላቀሉ ጥሪውን አስተላልፏል።

አሁን ላይ የተተከለው የሰላም ችግኝ፣ ነገ ለኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ የሁሉም ምኞት ነው።

የሰላም ስምምነቱን ሊያጣጥሉ የሚሞክሩም ትርፋቸው ግጭት ነውና፣ ሕዝቡ ሴራቸውን አውቆ እኩይ አላማቸውን ለማስቆም የሚችለውን በጎ ጥረት ሁሉ ሊያጠናክርም ይገባል።