Search

“የዓድዋ ጦርነት የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግል መጀመሪያ ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካ አንድነት መጀመሪያም ነው”

ዓርብ ኅዳር 26, 2018 126

ኢትዮጵያ አንድነትን፣ ነፃነትን እና ለፍትሕ መታገልን የምትወክል፤ በዓድዋ ድል በመንሳት የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግል የጀመረች ናት ሲሉ ለፓን አፍሪካ ንቅናቄ እና ለአፍሪካ ህብረት ምስረታ ጉልህ አበርክቶ ያደረጉ የአፍሪካ መሪዎች ልጆች እና የልጅ ልጆች ገለጹ።

የዓድዋ ድል መታሰቢያን በጎበኙበት ወቅት በተቋሙ ባሉ ቅርሶች ዙሪያ ገለጻና ማብራሪያ የተደረገላቸው እንግዶቹ፤ አባቶቻችን የቅኝ ግዛትን ታግለው ያገኙትን ፖለቲካዊ ነጻነት በኢኮኖሚው መስክም ልንደግመው ይገባል ብለዋል።

በጉብኝቱ የመጀመሪያው የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓትሪስ ሉሙምባ ልጅ፣ የመጀመሪያው የጋና ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህ ልጅ እና የልጅ ልጅ፣ የመጀመሪያው የዛምቢያ ፕሬዚዳንት ኬኔት ካውንዳ ልጅ፣ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ የልጅ ልጅ እና የመጀመሪያው የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት  ጁሊየስ ኔሬሬ ልጅ ተሳትፈዋል።

በተጨማሪምታዋቂው ደቡብ አፍሪካዊ ፀረ አፓርታይድ ታጋይ ስቲቭ ቢኮ ልጅ፣ ደቡብ አፍሪካዊው የቀድሞ ፀረ አፓርታይድ ታጋይና ሚኒስትር ዋልተር ሲሱሉ ልጅ፣ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ANC) ፕሬዚዳንት፣ የፀረ አፓርታይድ ፖለቲከኛና አክቲቪስት ኦሊቨር ታምቦ ልጅ እና ሌሎችም ተገኝተዋል።

የኬኔት ካውንዳ ስድስተኛ ልጅ ካዋቼ ካውንዳ፥ አባቶቻችን አፍሪካን ለማዋሀድ አልመው ሕልማቸው እስከአሁን ባይሳካም የሚችሉትን ሠርተው አልፈዋል ብለዋል።

ይህን ሕልም አሁን ያለው ትውልድ ካልተገበረው ሕልሙ ከእነርሱ ጋር እንደሚሞት ገልጸው፤ አባቶች ለዚህ በለኮሱት የነጻነት ችቦ ሀገራትን ከቅኝ ግዛት ነጥቀው ማውጣት መቻላቸውን ተናግረዋል።

አባቶቻችን ቅኝ ግዛትን ታግለው ያገኙትን ፖለቲካዊ ነጻነት በኢኮኖሚው መስክም ልንደግመው ይገባል ያሉት ካዋቼ ካውንዳ፤ አፍሪካ ብዙ ሀብት በእጇ እያላት ወደ ሌላ የምታይበት ምክንያት ሊኖር እንደማይገባ አመልክተዋል።

የፓትሪስ ሉሙምባ ልጅ ሮናልድ ሉሙምባ በበኩላቸው፤ የዓድዋ ጦርነት የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግል መጀመሪያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ አንድነትም መጀመሪያ መሆኑን ገልጸው፤ ይህን እውነታ ለልጆቻችን ማስተማር ይገባናል ብለዋል።

ሮናልድ ሉሙምባ በጉብኝታቸው መደሰታቸውን ገልጸው፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያን በአዲስ አበባ የሚያልፉ አፍሪካውያን በሙሉ ሊጎበኙት የሚገባ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የጁሊየስ ኔሬሬ ልጅ ማዳራካ ኔሬሬ፥ ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ያደረጉት ትግል የፓን አፍሪካኒዝም ዓላማን ቀጣይነት ያሳየ እንደሆነ አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ አንድነትን፣ ነፃነትን፣ ለፍትሕ መታገልን ትወክላለች ያሉት ደግሞ የአፍሪካ ሌጋሲ ፋውንዴሽን ዋና ጸሀፊ ሙሳ ኢብራሂም ጋዳፊ ናቸው።

ወጣት ኢትዮጵያውያን ሴቶች እና ወንዶች ንቁ፣ በተስፋና በሕልም የተሞሉ እንደሆኑ ማስተዋል መቻላቸውንም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ያለውን የነፃነት ታሪክ ከአህጉሪቱ ሌላ ክፍል ካለው የነፃነት ታሪክ ጋር ለማገናኘት ትልቅ ፍላጎት እንዳላቸውም ነው የገለጹት።