ከ39 ኮርሶች 25ቱን ‘A+’ በማስመዝገብ አጠቃላይ 4.00 ነጥብ በማምጣት የተመረቀው የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የ2018 ዓ.ም የምረቃ ድምቀት ተማሪ ቶልቻ ከበደ ሆኗል።
የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 089 ተማሪዎች ዛሬ አስመረቋል።
በዛሬው የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የምረቃ ሥነ ሥርዓት 1 ሺህ 089 ተማሪዎች ከተመረቁበት ውስጥ፣ በነርሲንግ ሙያ የትምህርት ውጤቱ አራት ነጥብ በማምጣት ትኩረት የሳበው ተማሪ ቶልቻ ከበደ የዓመቱ የዋንጫ እና ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
በነርሲንግ የትምህርት መስክ የተመረቀው ቶልቻ፣ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ከወሰዳቸው 39 ኮርሶች መካከል 25ቱን ‘A+’ እንዲሁም የተቀሩትን ኮርሶች ‘A’ በማምጣት ሙሉ 4.00 ውጤት (CGPA) ማስመዝገብ ችሏል።
ይህ አስደናቂ ውጤት ተማሪውን በከፍተኛ ማዕረግ እንዲመረቅ ከማስቻሉም በላይ፣ የ2018 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲው ኮከብ ተማሪ እና የዋንጫ እንዲሁም የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ እንዲሆን አድርጎታል።
ተማሪ ቶልቻ በባሌ ዞን ጋሠራ ወረዳ ተወልዶ ያደገ ሲሆን፣ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በከፍተኛ ውጤት አጠናቋል።
ለስኬቱ መሠረት የሆነው ለትምህርቱ የሰጠው ልዩ ትኩረት፣ ትጋት እና ተከታታይ ጥረት መሆኑን የገለጸው ቶልቻ፣ ከልጅነቱ ጀምሮ የደረጃ ተሸላሚ እንደነበር እና በትጋት በመማሩ ለዚህ ውጤት መብቃቱን ተናግሯል።
“የወላጅ እናቴና አባቴ እንዲሁም ከመምህሮቼ ያገኘሁት ድጋፍ ለውጤቴ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል” ሲልም ገልጿል።
ወደፊት በተማረው የጤና ሙያ መስክ ሀገሩን በቅንነትና በርኅራኄ ለማገልገል ቁርጠኛ መሆኑን ተናግሯል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።