Search

የባሕር በር ጥያቄ ከየብስ ጥገኝነት ወደ ሰማያዊ ኢኮኖሚ

ቅዳሜ ሰኔ 20, 2018 88

የባሕር በር ጥያቄ ትልቁ ስኬት በሀገራችን ሥነ-ልቦና ውስጥ የፈጠረው የባሕር ላይ ንቃተ ህሊና ማደግ ነው።

ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል ኢትዮጵያ ባሕር በር አልባ ሀገር መሆኗ የፈጠረባትን የሥነ-ልቦና ጫና በመስበር፣ አሁን ላይ እንደ ሀገር የባሕር ኃይልን እንደገና ከማደራጀት ጀምሮ በዓለም አቀፍ የባሕር ላይ ትራንስፖርት እና ደኅንነት ውስጥ ቀጥተኛ ተዋናይ የመሆን ህልም የትውልዱ አዲስ መነሳሻ ሆኗል።

ይህ ለውጥ ዜጎች ስለ ሀገራቸው ዳር ድንበር አና ምጣኔ-ሀብታዊ ነፃነት ያላቸውን አመለካከት ከየብስ ወሰን በማውጣት፣ ወደ ሰፊው ዓለም አቀፍ የውኃ አካላት እንዲሻገር እያደረገ ይገኛል።

የባሕር በር ፍለጋው ከንግድ መስመርነት ባለፈ ከሀገራችን የወደፊት የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት እና የሎጂስቲክስ ምህንድስና ጋር የተያያዘ ነው።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የገነባቻቸው ግዙፍ የኢንዱስትሪ ማዕከላት እና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ እና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በሌሎች ሀገራት ወደቦች ፍቃድ እና ታሪፍ ላይ ብቻ ጥገኝነት የሌለው አስተማማኝ መውጫ ያስፈልጋቸዋል።

የራስን የባሕር በር አማራጭ መፍጠር ማለት፣ የኢንዱስትሪዎችን ኅልውና በአስተማማኝ መሠረት ላይ መገንባት እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ፍጥነት እንዲጎርፍ ማድረግ ማለት ነው።

ይህ አቀራረብ ንግድን ከሀገራዊ ደኅንነት ጋር አጣጥሞ የመጓዝ አዲስ ስትራቴጂካዊ ፍልስፍና ነው።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ ኢትዮጵያ ወደፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ትኩረት ለሚሰጠው "ሰማያዊ ኢኮኖሚ" (Blue Economy) ተጠቃሚ እንድትሆን በር የሚከፍት ነው።

የባሕር በር ማግኘት ማለት ዕቃ መጫኛ እና ማውረጃ ቦታ ማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ በባሕር ውስጥ የሀብት ቁፋሮ፣ የዓሣ ሀብት ልማት፣ የባሕር ላይ ቱሪዝም እና የባሕር ውስጥ የኬብል መሠረተ-ልማቶችን የመሳሰሉ እጅግ ግዙፍ የኢኮኖሚ አማራጮች ባለቤት መሆን ማለት ነው።

በመሆኑም የባሕር በር ጥያቄ ለአሁኑ ትውልድ የንግድ ማሳለጫ ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣዩ ትውልድ ሰፊውን የዓለም ሥነ-ምህዳር እና ምጣኔ-ሀብት በነፃነት እንዲቀላቀል የሚያደርግ የኢኮኖሚ ምሶሶ እና የሉዓላዊነት አዲስ መታወቂያ ነው።

በሔዋን ጌታቸው