Search

ዓድዋ የመላው አፍሪካውያን የድል ምልክት ሆኖ ይኖራል - የቀድሞው የጋና ፕሬዚዳንት ልጅ ሳሚያ ኩዋሜ ንክሩማ

ቅዳሜ ኅዳር 27, 2018 115

የዓድዋ ድል የመላው አፍሪካውያን የአሸናፊነት እና አንድነት ምልክት ሆኖ ይቀጥላል ሲሉ የመጀመሪያው የጋና ፕሬዝዳንት የኩዋሜ ንክሩማ ልጅ የሆኑት ሳሚያ ኩዋሜ ንክሩማ ተናገሩ፡፡
የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ የነበሩት የቀድሞው የጋና ፕሬዚዳንት ልጅ ሳሚያ ኩዋሜ ንክሩማ፤ ትናንትና ከሌሎች የፓን-አፍሪካን አቀንቃኝ ቤተሰቦች ጋር የዓድዋ ድል መታሰቢያ ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸው ወቅትም፤ የአሁኑ እና የወደፊቱ ትውልድ ስለ ዓድዋ ድል ፋይዳ በተሟላ ሁኔታ እንዲረዳና እንዲማርበት የተገነባው ይህ መታሰቢያ፣ እጅግ ጠቃሚና በከፍተኛ ሁኔታ የሚያነሳሳ ድንቅ ቅርስ ነው ብለዋል፡፡
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ራሷን ከቅኝ ግዛት ስጋትና ጥቃት የተከላከለችበት እንዲሁም ጥቁር ሕዝቦች ቅኝ ለመግዛት የመጣውን ወራሪ ኃይልን የመከቱበት የድል ምልክት መሆኑ ትልቅ ትርጉም አለው ሲሉ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግረዋል፡፡
ድሉ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በነቂስ ወጥተው በአንድ ልብ ቅኝ ለመግዛት የመጣውን የጣሊያን ወራሪ ጦር የመከቱበት የአንድነትና የፅናት ተምሳሌት ነው ሲሉም ገልጸውታል፡፡
የዓድዋ ድል የሁሉም አፍሪካውያን የድል ምልክት ሆኖ ወደፊትም ይኖራል ሲሉ ሳሚያ ንክሩማ አጽንኦት ሰጥተዋል።
አፍሪካውያን በአንድነት ስንቆም እና ስንተባበር በሁሉም መስኮች የቅኝ ግዛት አስተሳሰቦችን መግታትና ማሸነፍ እንደምንችል ዓድዋ ትልቅ መሰረት የጣለ ነው ብለዋል።
የዓድዋ ድል የአፍሪካውያን የስኬት ታሪክ በመሆኑ፤ ስለ ድሉ ለራሳችን፣ ለልጆቻችንና ለቀጣይ ትውልድ ማስተማር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
አፍሪካ አሁን ያለባትን ድህነትና ኋላቀርነት እንዲሁም የኢኮኖሚ መገለል የምታሸንፍበት አቅም እንዳላትም ሳሚያ ንክሩማ ተናግረዋል።
በላሉ ኢታላ