Search

ከግድቡ እስከ ወደቡ የዘለቀው የግብፅ ሀሰተኛ ውንጀላዎች

ቅዳሜ ኅዳር 27, 2018 60

ከሄሊዮፖሊስ ቤተ-መንግስት እስከ ዓለምቀፍ መድረኮች፤ ከግድቡ እስከ ወደቡ የዘለቁ ሀሰተኛ ውንጀላዎች ቀጥለዋል፡፡

የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሰጥቶ መቀበል እና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሰፍኑ ውይይቶች ላይ ከመገኘት ይልቅ እውነትነት የሌላቸው መረጃዎችን ለዓለም ህዝብ ማቀበል ምርጫቸው ሆኗል፡፡

ሆኖም ይህን የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው ብሎም እንደማትታገሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ ላይ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መግለጫ ላይ ትኩረቱን ያደረገው የኢቢሲ የሀገር ጉዳይ መሰናዶ ታሪካዊ ቅብብሎሽ የተላበሰው ከግድቡ እስከ ወደቡ የዘለቀው የግብፅ ተግባራት ላይ ውይይት አድርጓል፡፡

ግብፅ የዓባይ ግድብን በተመለከተ የተጠቃሚነት ጥያቄዋን አዋጭ እንደማይሆን ስትገነዘብ ኢትዮጵያ ለውኃ ክፍፍል አስተዳድር ብቁ አይደለችም በሚል ክስ ብቅ ስለማለቷ የኪንግስ ኦፍ ዓባይ ሚዲያ ሥራ አስኪያጅ ኡስታዝ ጀማል በሽር ገልፀዋል፡፡

የግድቡን መገንባት ተከትሎ “ለድርቅ ተጋላጭ እሆናለሁ” እና መሰል የውኃ እጥረት ጥያቄዎችን ስትሰነዝር የነበረችው ግብጽ፤ አሁን ላይ ከውኃ አለቃቀቅ ጋር ተያይዞ “ጎርፍ ያሰጋኛል”፤ የሚል የተጣረሰ ሀሳብን እያነሳች ስለመሆኑ አመላክተዋል፡፡

ይህን መነሻ በማድረግም የግድቡን ውኃ ማስተዳደር ላይ ድርሻ እንዲኖራት ፍላጎት ስለመኖሩ ገልፀው፤ ሀሳቡ ሉዓላዊነትን የሚጋፋ እና አግባብነት የጎደለው ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ኡስታዝ ጀማል አክለውም የኢትዮጵያ ብልፅግና የሚያሰጋት ግብፅ በቀጠናው በተለይም የኢትዮጵያ ውስጣዊ እና ውጫዊ ጉዳዮችን ዓይኗን ሳታራግብ የምታስተውለው በአካባቢው ልትፈጥር የምትችለውን ተፅዕኖ በማሰብ ስለመሆኑ ይገልፃሉ፡፡

ይህ የግብፅ የቅኝ ግዛት እሳቤ ከግድቡ እስከ ወደቡ አድጎ እያየነው ነው ያሉት ኡስታዝ ጀማል፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ መልስ እንዳያገኝ ከሀገር ውስጥ ባንዳዎችና ከውጪ ባዳዎች ጋር በጥምረት እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

ይህንንም ለማክሸፍ የተያዙ የውሃ እና የእርሻ ተኮር ስራዎችን ማጎልበት፣ የውስጥ አንድነትን ማጠናከር እንዲሁም የኢንደስትሪውን ዘርፍ ከውኃ ጋር ተያያዝ በማድረግ ተጠቃሚነትን ከፍ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ 

በአፎምያ ክበበው

#Ebc #Ebcdotstream #Ethiopia #GERD #seaaccess