የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር "ዴሞክራሲያዊ መግባባት፣ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ቃል በነገው ዕለት የሚከበረውን 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል አስመልክቶ በሆሳዕና የተዘጋጀውን ሲምፖዚየም በንግግር ከፍተዋል።
አቶ አገኘሁ በዚሁ ወቅት፥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል ዓላማ ሕዝቦች ተሰባስበው በመተዋወቅ የኢትዮጵያን ኅብረ ብሔራዊነት እንዲያጠናክሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
በዓሉ ላለፉት 19 ዓመታት ሲከበር ለዘመናት አብረው የኖሩት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይበልጥ መቀራረብ መቻላቸውን አንስተው፣ ኢትዮጵያውያን ጌጣቸን የሆነውን ኅብራችንን በማጠናከር ሀገራችንን ወደ ከፍታ ማማዋ እንመልሳት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አጠናቃ ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት በጀመረችበት ማግስት የሚከበር መሆኑ የዘንድሮውን በዓል ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

መጪው ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ዝግጅት ላይ በምንገኝበት ወቅት መከበሩም የበዓሉ ልዩ መገለጫ ነው ብለዋል አቶ አገኘሁ።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን የተጎናጸፈው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የበዓሉ አዘጋጅ መሆኑን ጠቅሰው፣ ክልሉ ዝግጅቱን በልዩ ሁኔታ በማከናወኑ አመስግነዋል።
ኢትዮጵያ ታላቅ ሕዝብ ያላት ሀገር መሆኗን ያወሱት አፈ-ጉባኤው፣ አሁን ያለው አመራር እና ትውልድም ይህን የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚያረጋግጥ ሥራ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በጥናት የዳበሩ ሥራዎች የሚቀርቡባበቸው እንደዛሬው ዓይነት ሲምፖዚየሞችን በዓመት አንዴ ብቻ ከማካሄድ ይልቅ በየጊዜው ለሕዝብ በማቅረብ ግንዛቤን ማስፋት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
ሆሳዕና የኅብረ ብሔራዊነት መናገሻ ነች ያሉት አቶ አገኘሁ፤ በከተማዋ በተዘጋጀው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ክብረበዓል በመታደማቸው የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታም ገልጸዋል።
በለሚ ታደሰ
#ebcdotstream #Ethiopia #nationalitiesday #hosaena