20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ስናከብር ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ሊያስጠብቅ የሚያስችል መደላድል በመፍጠር ሊሆን ይገባል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ ገለጹ።
"ዴሞክራሲያዊ መግባባት፣ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ቃል በነገው ዕለት የሚከበረውን 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ በሆሳዕና ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው።
አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ በሲምፖዚየሙ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክር፥ የዘንድሮው በዓል ከቀድሞዎቹ በተለየ ሁኔታ የሀገራችንን ገፅታ በሁለንተናዊ መንገድ የምናስተዋውቅበት መድረክ ነው ብለዋል።
እኛ ኢትዮጵያውያን የአይቻልም አስተሳሰብን በመስበር በላብ እና በደም ጠብታ የመላው ጥቁር ሕዝብ የኩራት ምንጭ የሆነውን ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ባስመረቅንበት እና ሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ባበሰርንበት ማግስት የምናከብረው በመሆኑ የዘንድሮው በዓል ይለያል ሲሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያዊነት ኅብረ ቀለም ማሳያ፤ የፍቅር፣ የአብሮነት እና የመቻቻል ተምሳሌት የሆነው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ኢትዮጵያዊነትን የምናጎላበት፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የምናጠናክርበት፣ የሕዝቦችን ዴሞክራሲ የምናጎለብትበት ትልቅ ሁነት ነው ብለዋል።
ዴሞክራሲያዊ ኅብረ ብሔራዊነታችን የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሥራችንን ለማፋጠን እንዲሁም ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት በማድረግ ከዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ትልቁ አቅማችን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በሜሮን ንብረት
#ebcdotstream #Ethiopia #nationalitiesday #hosaena