Search

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሕገ መንግሥታዊ ቃል ኪዳናችንን የምናድስበትና የብዝኃነታችንን ዐቅም የምናጎለብትበት ቀን ነው - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

እሑድ ኅዳር 28, 2018 79

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሕገ መንግሥታዊ ቃል ኪዳናችንን የምናድስበትና የብዝኃነታችንን ዐቅም የምናጎለብትበት ቀን ነው ሲል የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

አገልግሎቱ 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረ-ሰቦችና ሕዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፈው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ የሚገለጽ ብዝኃነት ባለቤት ናት። የቋንቋ፣ የባህል፣ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካዊ አመለካከት፣ የዕድሜ፣ የፆታ ወ.ዘ.ተ ብዝኃነቶቿ የሚያስጌጧት ድንቅና ቀደምት ሀገር ናት፤ ኢትዮጵያ።

ይህንን ብዝኃነቷን እንደ እሴት የምታዳብርበት፣ እሴቱን ወደ መፈጸም ዐቅም የምትለውጥበት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐት ባለቤትም ናት። ለዚህም ነው የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ በሆነው ሕገ መንግሥታችን አንድ የጋራ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት በነፃ ፈቃዳችን የተስማማነው።

ምንም እንኳ የሥርዐተ መንግሥት ታሪካችን በርካታ ሺህ ዓመታትን ቢያስቆጥርም ሕገ መንግሥታዊ ልምምዳችን ግን በበቂ ያልዳበረ፤ ከአንድ ክፍለ ዘመን ያልተሻገረ ነው። ለዚህም ነው የዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ግንባታ ሂደታችን በምንሻው ልክ ያልጎለበተው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐታችንን መሠረት ለማስያዝ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ስኬቶችም እየተመዘገቡ ይገኛሉ። ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩና እንዲጠበቁ፣ የግልጽነትና ተጠያቂነት ሥርዐት እንዲጎለብት፣ ገለልተኛ እና ጠንካራ ሀገራዊ ተቋማት እንዲፈጠሩ፣ የሕዝቦች የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ መንግሥት በልዩ ትኩረት እየሠራ፤ አስደማሚ ስኬቶችም እየተመዘገቡ ነው።

በሕገ መንግሥታችን ዕውቅና ያገኙ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአግባቡ እንዲከበሩና እንዲጠበቁ ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት እየተገነቡ ነው። ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲጎለብት ገለልተኛ የፍትሕ ሥርዐትን እውን ከማድረግ ባሻገር ብዝኃነትን የሚያስተናግድ ዓውድ ተፈጥሯል።

ኢትዮጵያውያን ባህላቸውን፣ ትውፊታቸውን፣ ማንነታቸውን፣ መሻታቸውን የሚያስተዋውቁበት ሥርዐት በሕገ መንግሥታችን እውን የሆነበትን ኅዳር 29 ቀን በየዓመቱ በልዩ ልዩ ኹነቶች እያከበርነው፤ የእርስ በርስ ትውውቃችንን እያጠናከርንበትና የበለጠ አንድነታችን እያዳበርንበትም እንገኛለን።

በበዓሉ የብዝኃነታችንን ዐቅም አልቀን አሳይተናል። የሕዳሴ ግድባችንን እውን ለማድረግ የሚያስችል ገንዘብ ለማሰባሰብ የተጠቀምንበትም ይህንን በዓላችንን ነበር። በውጤቱም ሕዳሴን አሳክተን ብዝኃነታችን ዐቅማችን እንደኾነ አረጋግጠንበታል። የወል የድል ታሪክ አስመዝግበንበታል።

ኢትዮጵያ ብዝኃነቷን የሚያስተናግድ ሥርዐት ዘርግታለች። ብዝኃነት ጌጧ እና ዐቅሟ መሆኑንም ተገንዝባለች። ለዚህም ነው ከለውጡ ማግሥት የኢትዮጵያ ጉዞ በብርሃን፣ መዳረሻዋም ብልጽግና ሆኖ እየታየ ያለው።

በውስጥ ባንዳዎች እና በሩቅ ባዕዳን ሴራ ልዩነታችን መለያያችን ሆኖ ለዘመናት ተቀንቅኗል፤ አብሮነታችን ሲፈታተንና ከስኬታችን ሲጎትትም ኖሯል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሕዝባችን ይህንን ተገንዝቧል። የኢትዮጵያ መሻት፣ ትልምና ብልጽግና በአብሮነት እንደሚረጋገጥ፤ አብሮነታችን በብዝኃነታችን እንደሚያጌጥ፤ ብዝኃነታችን ዐቅማችን መሆኑን ተገንዝበናል። ዴሞክራሲያዊ መግባባት እና ሕገ መንግሥታዊነት ደግሞ መንገዶቻችን ናቸው።

ለዚህም ነው “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልእክት የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን እያከበርን የምንገኘው።

እንኳን ለ20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን አደረሳችሁ!