Search

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተከበረ

እሑድ ኅዳር 28, 2018 71

20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በቻይና ቤጂንግ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።
በዓሉን አስመልክቶ በተዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ፣ የሚሲዮኑ አመራሮችና ሠራተኞች፣ በቻይና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አመራሮችና አባላት፣ በተለያዩ የቻይና ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም በቤጂንግ የውጭ ግንኙነት ዩኒቨርስቲ የአማርኛ ቋንቋ ተማሪዎች ተገኝተዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳና በቻይና የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ተፈራ ደርበው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ በርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ብዝኃነትን ተላብሰው ልዩነታቸው ሳይገድባቸው በአብሮነት የሚኖሩባት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
 
ይህንን የብዝኃነት ውበት ይዞ ለዘመናት የዘለቀውን አብሮነት በማስቀጠል፣ ኅብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያ ይበልጥ የበለፀገች እና ተደማጭ እንድትሆን ቃል የምንገባበት ቀን ሊሆን ይገባል ብለዋል።
አምባሳደር ተፈራ አያይዘውም፤ ልዩነቶቻችን ኅብር ሆነው እንዲቀጥሉ የረዱንን የመቻቻል እሴቶች ከመጠበቅ ባሻገር፣ ዴሞክራሲያዊ መግባባትን ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰር የፌዴራል ስርዓቱን ማጠናከር ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
በበዓሉ ላይ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ሃሳቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ተሳታፊዎቹ ብዝኃነት ውበት ብቻ ሳይሆን ጉልበትም ጭምር መሆኑን ጠቅሰው፤ የእያንዳንዱን ብሔር ብሔረሰብ እና ሕዝብ እሴት በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ የኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን የልማት ግስጋሴና ሁለንተናዊ ዕድገትን ማስቀጠል እንደሚቻል አመላክተዋል።
ለዚህ ስኬት ደግሞ ሀገራዊ መግባባት ቁልፍ መሆኑን በማንሳት፣ ዘመኑን የዋጀና ሀገር በቀል ኅብረ ብሔራዊ ዴሞክራሲን ማራመድ እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተዋል።
በዓሉን ድምቀት የሚሰጡ የባህላዊ ቡና ስነ-ስርዓት እና ኅብረ ብሔራዊ ሙዚቃዎች ለታዳሚው ቀርበዋል። ከዚህም በተጨማሪ በቻይና የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ልጆች መዝሙር ያቀረቡ ሲሆን፤ የቻይና የውጭ ግንኙነት ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ተማሪዎችም የግጥም ዝግጅት ለታዳሚዎች አቅርበዋል።
ነፃነት ክንፈ (ከቤጂንግ - ቻይና)