ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል የማጠቃለያ መርሐ ግብር ዛሬ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ሆሳዕና ከተማ ተከናውኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመድረኩ ያስተላለፉት መልዕክት ሀገርን ወደላቀ ደረጃ የሚያሻግሩ ሀሳቦችን የያዘ ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ በላይ ወዲሻ ገልጸዋል።
አቶ በላይ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ፥ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዕለቱን ሲያከብር በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ በመግባባት እና የኢትዮጵያን አንድነት በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሁሉም የየራሳቸው ማንነት እና መገለጫ ያሏቸው በመሆኑ፤ አንዱ የሌላውን ባህል ማወቅ እና መረዳት ይጠበቅበታል ብለዋል።
በዓሉ መከበሩ አንዱ ብሔር የሌላውን ባህል በማክበር ተግባቦትን ለመፍጠር፣ ወንድማማችነትን ለማጠናከር እንዲሁም ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ጉልህ አበርክቶ እንዳለውም ተናግረዋል።
ብሔራዊ ማንነት እና ሀገራዊ ማንነት ላይ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከትን በመፍጠር ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታልም ነው ኃላፊው ያሉት።
በዓሉ በየክልሉ መከበሩም የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከማገዙም ባሻገር ክልሎቹ የተለያዩ መስህቦቻቸውን እንዲያስተዋውቁ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #NNPDay