Search

ከሀገራችን ባህልና ሥነ-ምግባር ያፈነገጠ አስነዋሪ አለባበስ ለብሰው ለሕዝብ የታዩ እና ያሰራጩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ማክሰኞ ኅዳር 30, 2018 89

ከሀገራችን ባህልና ሥነ-ምግባር ያፈነገጠ አስነዋሪ አለባበስ ለብሰው በአደባባይ እና በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ለሕዝብ የታዩ ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ፖሊስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው በ3ኛው የጂ ፓወር ቲክቶክ ክሬቲቭ አዋርድ (G-Power TikTok Creative Award) ላይ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ባህልና ሥነ-ምግባር ባፈነገጠ አኳኋን ሰውነታቸውን የገላለጠ አለባበስ ለብሰው በአደባባይና በቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት ለሕዝብ የታዩ ተጠርጣሪዎችን ከነግብረ-አበሮቻቸው በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ ማጣራት መጀመሩን አስታውቋል።
ፌደራል ፖሊስ እነዚህን ግለሰቦች እንዲሁም ዝግጅቱን በስፖንሰርነት የደገፉና ፕሮግራሙን ያቀነባበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።
‎በቁጥጥር ሥር የዋሉት፡-
‎1ኛ. ወንጌላዊት ገብረ እንድርያስ በርሄ፣
‎2ኛ. በርከት ፀጋዬ ጅፋር፣
‎3ኛ. መቅድም ደረጄ መንግስቱ፣
‎4ኛ. ግሩም ገዛሀኝ ቀጭኔ እና
‎5ኛ. ዮሃንስ መኮንን ሀ/ማርየም ‎የተባሉ ግለሰቦች መሆናቸውን ፖሊስ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከህብረተሰቡ ባህልና እሴት ያፈነገጡ አለባበሶችና መጤ ባህሎች ተስፋፍተው በትውልዱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያስከትሉ፣ ተጠርጣሪዎቹ ላይ የሕግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የጀመረውን ምርመራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም በመረጃው አስታውቋል።