Search

የኢትዮጵያ ድምቀት የሆነው ኅብረ ብሔራዊ ክልል - ማዕከላዊ ኢትዮጵያ

ማክሰኞ ኅዳር 30, 2018 29

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሕገ መንግሥቱ መሠረት የክልልነት ዕውቅናውን አረጋግጦ የተመሠረተው ነሐሴ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ነው።

ክልሉ ጉራጌ፣ ሀዲያ፣ ስልጤ፣ ከምባታ፣ ሀላባ፣ የም፣ ጠምባሮ፣ ቀቤና፣ ማረቆ እና ዶንጋ የተሰኙ አስር ብሔረሰቦች ተከባብረው በአንድነት የሚኖሩበት በሕብር የደመቀ ክልል ነው።

በሰባት ዞኖች፣ በ3 ልዩ ወረዳዎች፣ በ50 ወረዳዎች እና በ29 የከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረ እንደሆነም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የመደመር መንግሥት ራስን በራስ የማስተዳደር ትክክለኛ ምላሽ ማሳያ የሆነው ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት ባሳየው ጥረት በሁሉም ዘርፍ አስደናቂ ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል።

በተፈጥሮ ሀብት እና በቱሪዝም መስህቦች የታደለው ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በመደመር ኢትዮጵያን ወደ ልዕልናዋ ማማ ለማድረስ እየተጋ ይገኛል።

ብዝኃነትን በውስጡ የያዘው ክልሉ የራሳቸው የተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ፣ የቤት አሠራር፣ ባህላዊ ዳኝነት እና የእርቅ ሥነ-ሥርዓት፣ ሥራ ፈጣሪነት እና ታታሪነት፣ ጀግንነት፣ የቁጠባ እና መረዳዳት ባህል ያላቸው ብሔረሰቦች በጋራ ተሰናስለው የሚኖሩበት የኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊነት ተምሳሌት ነው።

የክልሉ ብሔረሰቦች ታታሪነት ከክልሉም አልፎ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የደረሰ ሲሆን፣ ከክልሉ የተገኙ ኢትዮጵያውያን በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ጠንክረው ሠርተው ሀብት በመፍራት ይታወቃሉ።

በሁሉም የክልሉ ብሔረሰቦች የሚታወቅ እና ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚወዱት እንሰት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በረከት ሲሆን፣ የክልሉ መንግሥትም ይህን የጋራ መገለጫ እንደ ዓርማው አየተጠቀመው ይገኛል።

እምቅ የቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት አቅም፣ የሃይማኖት ብዝኃነት እና ጥንታዊ የሃይማኖት ቅርሶች፣ የባህላዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት እና እምቅ የማዕድን ሀብት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ትሩፋቶች ናቸው።

ለበርበሬ እንደ መለያ የሚጠራው እና በመላው ኢትዮጵያ የሚወደደው የማረቆ በርበሬ መገኛ የዚሁ ክልል ማረቆ ልዩ ወረዳ ነው።

እንደነ ሌተናል ጄኔራል ወልደሥላሴ በረካ እና የአየር ኃይሉ ወደር የለሽ ጀግና ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስን በማበርከት ለኢትዮጵያ አንድነት መሥዋዕትነት የከፈለ ጀግና ሕዝብ ያለበት ነው።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራ ያለው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነታቸው መቼም የማይደራደሩ ፓለቲከኞች፣ ዲፕሎማቶች፣ ምሁራን እና ጉምቱ ባለሀብቶችን ለኢትዮጵያ አበርክቷል።

ቅንነት፣ ግልጽነት እና የሀገር ፍቅር ባህሉ የሆነው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬም በየዘርፉ ኢትዮጵያን እየገነቡ ያሉ ልጆች አሉት።

ከከልሉ እና ኢትዮጵያ አልፎ የዓለም ሀብት የሆነው ጢያ ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኝ የክልሉን ሕዝብ የረጅም ዘመን ሥልጣኔ ማሳያ ቅርስ ነው።

ቆጠር ገደራ ጥብቅ የተፈጥሮ ደን፣ መጨፈራ ሐይቅ፣ አባያ ሐይቅ፣ ሐር ሼይጠን እና ጊቤ ሸለቆ ሰው ሠራሽ ሐይቅ በክልሉ የሚገኙ ውብ የተፈጥሮ ሀብቶች ናቸው።

የተለያዩ አእዋፋት እና የዱር እንስሳት የሚገኙበት የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ክልሉ የሚደምቅበት ሌላው የቱሪዝም ሀብት ነው።

ሀምበርቾ 777 ሲደመር ከከልሉ ልዩ ውበቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ አርቶ ፍል ውኃም ተቆጥረው ከማያልቁት የክልሉ ሀብቶች መካከል ይገኛል።

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሮዝመሪ፣ በርበሬ፣ ዝንጅብል እና ሌሎች ቅመማ ቅመሞችን በማምረት ኢትዮጵያን የሚያጣፍጥ ክልል ነው።

ቀድሞውንም እንደ ‘ጀፎረ’ ባሉ ውብ ሰፈሮቹ የገጠር ኮሪደር ልማትን ለረጅም ዘመናት ተግባር የኖረው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ የሆነውን የገጠር ኮርደር ልማት ማሳያ የሆኑ ውብ መንደሮችን በሀዲያ፣ ሀላባ እና ከምባታ ዞኖች በመገንባት ተሞክሮውን አሳይቷል።

በአስተዳደር ማዕከል ረገድ የብዝኃ ከተሞች አቅጣጫን የሚከተለው ክልሉ፣ ሆሳዕና፣ ወልቂጤ፣ ወራቤ፣ ቡታጅራ፣ ሀላባ ቁሊቶ፣ ዱራሜ እና ሳጃ ከተሞችን እንደ ክልል ማዕከል ከተሞች እየተጠቀመ ይገኛል።

ሆሳዕና የክልሉ የፖለቲካ አስተዳደር ከተማ ስትሆን 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር ብረሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓልን በድምቀት አስተናግዳለች።

የኢትዮጵያ አንድነት መከታ የሆኑትን ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስን ለኢትዮጵያ ያበረከተችው ውቧ ሆሳዕና ከመላው ኢትዮጵያ ከተሰባሰቡት የኢትዮጵያ ልጆች ጋር በበዓሉ ደምቃ አሳልፋለች።

በለሚ ታደሰ

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #CentralEthiopiaRegion #Hosaena #NNPDay