Search

የአዲስ አበባ አስደማሚ ለውጥ - በኬኒያዊዋ ፀሐፊው ዕይታ

ማክሰኞ ኅዳር 30, 2018 142

ውድ ኬኒያውያን ሲል የሚጀምረው ፅሑፉ፣ በእናት ቤት የተዘጋጀ ምግብ ምርጡ ምግብ እንደሆነ ማንም ሰው ይናገራል፤ይህ ግን ዕውነት የሚሆነው የኬኒያን ምድር ለቃችሁ አዲስ አበባ እስክትገቡ ነው ይላል።
‎የአዲስ አበባ ምግብ ጣፋጭና ተናፋቂ እንደሆነ ኬንያዊቷ የዘ-ስታንዳርድ አምደኛ ዚ አኒያንጎ ትመሰክራለች።
‎የተንጣለለው ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ስፋቱ አስገራሚ ነው ስትል የምትገልጸው ፀሐፊዋ፤ "ባማረው የአዲስ አበባ ጎዳና ስትዘዋወሩ ቀዝቀዝ ያለው አየር ይቀበላችኋል፤ የናይሮቢ የአየር ሁኔታ ይሻላል የሚል ሃሳብ ቢመጣባችሁም፤ በዚህ ግን ምንም ዓይነት መጥፎ ጠረን የለም" ትላለች፡፡
‎ፀሐፊዋ ተዘዋውራ በተመለከተቻቸው የአዲስ አበባ አካባቢዎች በየቦታው የተደፋ ቆሻሻ፣ ከየምሽት ክለቡ በፉክክር መልክ የሚለቀቅ የጆሮን ታምቡር የሚበጥስ ድምፅ እና በተሽከርካሪ ብዛት የተጨናነቁ መንገዶች እንደማይታዩ ነው የምትገልጸው።
‎አዲስ አበባ ላይ በርግጥ የኬኒያን ኪስዋህሊ ቋንቋ የሚናገር ሰው ማግኘት አይቻልም፤ ከዚህ ውጪ ግን በህብረ ቀለማት ያሸበረቁና በሙዚቃ ስልት የሚደንሱ ፋውንቴኖች አስደማሚ ናቸው። ንፁህ መንገድ ፅዱ አካባቢ ተፈጥሯል ትላለች ፀሐፊዋ።
‎ነዋሪው የአካባቢውን ንፅህና ያስጠብቃል። አረንጓዴና ውበት ያላቸውን ዛፎች በየመንገዱ ማየት የተለመደ ነው። በዚህም አዲስ አበባ የእርጋታና የሰላም ምልክት መሆን ችላለች። አካባቢን ማበላሸት ከፍ ላለ ቅጣት ስለሚዳርግ የተበላሸ ነገር አይታይም ስትል አስፋራለችል።
‎ለአዲስ አበባ ከተማ እንዲህ መዋብ አንዱ ምስጢር ራሳቸውን የሰጡ ከፍተኛ የሥራ ትጋት ያላቸው ሴቷ የከተማ ከንቲባ ድርሻ የላቀ እንደሆነ በፅሑፉ አፅንኦት ተሰጥቶታል።
‎ከንቲባዋ በከተማዋ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲመዘገብ ማስቻላቸውንም ተጠቅሷል።
‎በአዲስ አበባ ያልተበከለ ከተማ መፍጠር የሚለው ከመፈክር አልፎ ህዝቡ በተግባር እያጣጣመው እንደሚገኝም በፅሑፉ ተብራርቷል።
‎በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) የገንዘብ ድጋፍ ሳይሆን በግብር ከፋዩ ዜጋ ገንዘብ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን እየተገነባች ትገኛለች የምትለው ፀሐፊዋ፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በዜጎች ገንዘብ የተገነባ ስለመሆኑም አያይዛ ገልጻለች።
ኬኒያ ከዚህ ትምህርት መውሰድ እንዳለባት በቁጭት ሃሳቧን የገለፀችው ኬኒያዊዋ ፀሐፊ፤ አንድ ሀሳብ በማንሳት የሀገሯን ዜጎች ትሞግታለች።
‎"የምርጫ ተወዳዳሪዎች ፤ 'በቀጣይ አምስት ዓመታት ሃገራችን ሲንጋፖርን መሆን አለባት' ሲሉ ይደመጣሉ እኔ ግን "ያ ቀርቶብን መጀመሪያ እንደ ኢትዮጵያ እንሁን" ስትል የአዲስ አበባን ሁለንተናዊ ለውጥ ከናይሮቢ ጋር ያወዳደረችበትን ፅሑፍ አጠቃልላለች።
‎በሲሳይ ደበበ