Search

በተሳሳተ መንገድ ትጥቅ ይዘው ጫካ ገብተው የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪውን እየተቀበሉ ነው

ረቡዕ ታኅሣሥ 01, 2018 62

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ፣ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሰላም ሂደቱ ውጤት እያሳየ ይገኛል።
ይህንኑ የሰላም ስምምነት መሠረት በማድረግም በተለይ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አመራሮች እና አባላት የሰላም አማራጭን በመቀበል ትጥቃቸውን አስረክበዋል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት በዞኑ በወገራ፣ በጭልጋ እና በኪንፋዝ ወረዳዎች እንዲሁም በጎንደር ከተማ እና አካባቢው ይንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ ታጣቂዎች ለሕዝብ እና ለሀገር ሰላም ሲሉ የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው ሰላምን መርጠዋል።
በተለይም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በወገራ ወረዳና አካባቢው እራሱን ጎንደሬ በጋሻው እያለ የሚጠራው ቡድን አባል የነበሩ በርካታ ታጣቂዎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ ተቀብለዋል።
በወገራና ኪንፋዝ ወረዳዎች አዋሳኝ ቀበሌዎችም በርካታ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን በመቀበል ትጥቃቸውን አስረክበዋል።
በተመሳሳይ በጭልጋ ወረዳም በጫካ የነበሩ ታጣቂዎች የመንግሥትን የሰላም አማራጭ ተቀብለው መግባታቸውን የወረዳው አስተዳደር አረጋግጧል።
ታጣቂዎቹ ለምን ሰላምን መረጡ?
ወደ ሰላማዊ ሕይወት የተመለሱት አካላት ውሳኔውን የወሰኑበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ የትጥቅ ትግሉ ያስከተለውን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ በግልጽ አስቀምጠዋል።
“የተሳሳተ መንገድ መርጠን ትግል ጀምረን ነበር" ያሉት ታጣቂዎቹ፣ ግጭቱ የሀገር ሀብትን ከማውደም፣ ሕጻናትን ከትምህርት ገበታ ውጭ ከማድረግ እንዲሁም እናቶችና ሴቶችን ለከፋ ችግር ከመዳረግ ውጭ ምንም ትርፍ እንደሌለው በመረዳታቸው የሰላም አማራጭን መከተላቸውን ተናግረዋል።
አክለውም፤ ከዚህ ቀደም በሰላም እጦት ምክንያት በሕዝቡ ላይ የደረሱ በደሎችን ለመካስና ያለፈውን ቁርሾ ለማረም፣ በቀጣይ ከሕዝቡ እና ከመንግሥት ጎን በመሆን ለልማትና ለዘላቂ ሰላም በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።
 
የመንግሥት እና የጸጥታ አመራሮች መልዕክት
ሰላምን የመረጡትን ታጣቂዎች የተቀበሉት አመራሮች፣ ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለ አጽንኦት ሰጥተው፤ የሰላም እጦት የፈጠረውን ክፍተት በመልካም ሥራ እንዲከሱ ጥሪ አቅርበዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አቶ አወቀ አስፈሬ፣ "የሰላም ስምምነቱን መሠረት በማድረግ መምጣታችሁ ለአካባቢያችሁ ሰላምና ልማት ያላችሁን ተነሳሽነት ያሳያል" ሲሉ፣ በሀገር መከላከያ የ13ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ሻምበል አስማረ በበኩላቸው፣ "በጫካ መኖር እጣ ፈንታው ሞት ነው፤ አሁን የሰላም ጥሪን ተቀብላችሁ መግባታችሁ ትክክለኛ ውሳኔ ነው" ብለዋል።
በመጨረሻም፣ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች ነፍጥ አንግበው የሚታገሉ አካላት በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም ስምምነት እድል በመጠቀም፣ ለአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ ለመፈለግ የሰላም አማራጩን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቀርቧል።