ዓባይ ከኢትዮጵያ ተራሮች አፈሩንም፣ ግንዱንም፣ ወርቁንም አግበስብሶ በሱዳን አልፎ ወደ ግብፅ ያመራል። አሰንብቱኝ ቢላቸው ችላ የሚሉትን ካርቱሞች በቁጣው ጎርፍ እያስፈራራ ቤት ለእንግዳ ብለው ወደሚጠብቁት ካይሮዎች ይገሰግሳል።
በተረቱ እና እንጉርጉሮው ብቻ የሚሸኙትን ኢትዮጵያውያንን አኩርፎ ለም አፈሩን እና ወርቁን፣ ሆድ ሲብሰው ደግሞ ግንዱን አገላብጦ ይዞ በመሄድ እንደ ንጉሥ ለሚጠብቁት ግብፆች በረከቱን ሲቸራቸው ኖሯል።
ግብፅም ውለታውን ታውቃለች እና “የዓባይ ልጅ ነኝ” ብላ ስሟን በስሙ እስክትቀይር የደረሰ ቁርኝት ፈጥራ በረከቱን ስታፍስ ለዛሬ ደርሳለች።
ለዚህም ነው ዓባይ የጥንቷ ግብፅ የሥልጣኔ ምንጭ እና ሕይወቷ ነው የሚባለው። ከኢትዮጵያ ተራሮች ለም አፈሩን አግብሰብሶ በረሃማውን የግብፅ መሬት የሚያረሰርሰው ዓባይ ባይኖር ከዓለማችን ቀደምት ሥልጣኔዎች አንዱ የሆነው የተራቀቀው እና የተማከለው የጥንቷ ግብፅ ማኅበረሰብ ሥልጣኔ ባልኖረ ነበረ።
ከሰኔ እስከ መስከረም ካለው ዓመታዊው የኢትዮጵያ የዝናብ ወቅት ማብቂያ ጊዜ ጀምሮ ያለው ወቅት ለግብፆች የዓመቱ የመጀመሪያ ወቅታው ሲሆን፣ "አኬት" ብለው ይጠሩታል። ይህ ወቅት ታዲያ እንግዳቸውን በጉጉት የሚጠብቁበት ነው።በጉጉት የሚጠብቁት እንግዳቸው ዓባይ ከኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች የሰበሰበውን በሚሊዮን ቶን የሚቆጠር በንጥረ-ነገር የበለፀገ ጥቁር ደለል በገጸ በረከት ያቀርብላቿል። ግብፃውያን ይህን ለም አፈር "ኬሜት" ወይም ጥቁር መሬት ብለው ይጠሩታል።
የግብፅ ገበሬዎች ለሙን አፈር እና ውኃውን በመጠቀም ስንዴ፣ ገብስ እና ተልባ ያሉ ዋና ዋና ሰብሎችን በገፍ ያመርታሉ። ይህም ግብፅ ከራሷ አልፋ ትርፍ ምርት እያመረተች ወደ ውጭ እንድትልክ አስችሏታል። ብልጧ ግብፅ ታዲያ በኢትዮጵያ አፈር እና ውኃ የምታመርተውን ጣፋጭ ብርቱካንም ወደ ዓባይ እናት በመላክ በውድ ትሸጣለች።
ወንዙ የጥንቷ ግብፅ ዋና የግንኙነት እና የንግድ ደም ቧንቧ የነበረ ሲሆን፣ ይህም ግብፅ የተዋሃደ መንግሥት እንድትመሰርት አስችሏታል። ከሰሜናዊ ግብፅ ወደ ደቡባዊ ግብፅ ለሚደረገው ጉዞ የዓባይ ወንዝ ዋነኛው የመጓጓዣ መስመሯ ነበር። ካይሮ እና ሌሎች ከተሞቻቸው ደግሞ ንፁህ የዓባይ ውኃን ይጠጡታል ይዝናኑበታልም። ለዚህም ነው የግብፅ ፈርኦኖች እንደ ካይሮ፣ ሜምፊስ እና ቴብስ ያሉ ጥንታዊ ከተሞቻቸውን በዓባይ ዳር የመሰረቱት።
12 ወራት ባለው የዘመን አቆጣጠራቸው አኬት፣ ፔሬት እና ሸሙ የተባሉ ሦስት ዋና ዋና ወቅቶች ያሉአቸው ግብፃውያን የዓባይ ውኃ ጎርፍ አስከትሎ ቢያጥለቀልቃቸው እንኳን እንደ ጥጋብ ዘመን ምልክት ወስደውት አምላካቸውን ያመሰግኑበታል እንጂ አይማረሩበትም።
የጥንታውያን ግብፆች መጻፊያ የሆነው ሄሮግሎፊክስ የሚሠራበት ፓፒረስ የሚበቅለው በዓባይ ዳርቻ ነው። ከ3 ሺህ ዓመታት በላይ ለቆየው ሥልጣኔያቸው ምንጭ በመሆኑ ነው ሄሮዶተስ ገብፅን "የዓባይ ወንዝ ስጦታ" ያላት።
“የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው”
ለዓባይ ጠብታ ውኃ የማታበረክተው ግብፅ ዓባይን እንዳሻት ስታዝዘው ኢትዮጵያ ግን ዓባይን እንዳትነካ ሴራ ስትጎነጉን ኖራለች። ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያን ከዓለም በመቆራረጥ ባይተዋር ልታደርጋት እንቅልፍ አጥታ የኖረችው ግብፅ እንግሊዝን ስታገኝ ደግሞ ተንኮሏን አዘመነችው። በጌታዋ ላይ በመተማመን ኢትዮጵያን ለመውረር ተደጋጋሚ ሙከራ ብታደርግም ገና ድንበር ሳትሻገር የኢትዮጵያውያንን ነበልባል ክንድ ቀምሳ ተመልሳለች።
አልሳካላት አለ አንጂ የወረራ ሙከራውም ሆነ የሁሉም ሴራዎቿ ማጠንጠኛ ደግሞ የዓባይን ምንጭ መቆጣጠር ነበር። ያሰበችው ሙሉ በሙሉ ባይሳካላትም ግን በረቀቀ ሴራዋ ኢትዮጵያውያን ለም አፈራቸውን ጠርጎ በደጃቸው የሚያልፈውን ውኃ እያዩ ሲቆዝሙ እንዲኖሩ የራሷን አስተዋጽኦ አድርጋለች።
ዓባይ ጥቁሩን አፈራቸውን ጭኖ ለግብፅ በረከት ማቅረቡ ያንገበገባቸው ኢትዮጵያውን “የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው” የሚል ቁጭት ወለድ ምሳሌያዊ አነጋገር ፈጥረዋል። በእርግጥ ይህ ተረት ለዓባይ ውኃ ብቻ ሳይሆን አረንጓዴ መሬት ይዘን ለመራባችንም የተነገረ ይመስላል።
ደግሞ ዓባይ ማደሪያ አጥቶ እንደከፋው ለማሳየትም “ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” ይላሉ ስሜታቸውን በምሳሌያዊ አነጋገር የመግለጽ ነባር ልማድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን። እርግጥ ዓባይም “ቤት የእግዜር ነው” ብለው መንገደኛን የሚያሳድሩት እንግዳ ተቀባይ ኢትዮጵያውያን አሳድሩኝ ብሎ ሲያስገመግም ጆሮ ስላልሰጡት ይመስላል ተበሳጭቶ ግንዱን እያገላበጠ የነጎደው። ቤተኞቹ ባይተዋር ያደረጉትን ዓባይን ታዲያ የሩቆቹ ግብፆች ለክብር እንግዳ የሚደረገውን ልዩ መስተንግዶ ሲያደርጉለት ላለፉት 3 ሺህ ዓመታት ኖረዋል።
ለባይተዋሩ ዓባይ ማደሪያ ለማግኘት የተደረጉ ሙከራዎችን ገጸ በረከቱን የለመደችው ግብፅ እያሰናከለች ብትኖርም እንጉርጉሮውን እና ቁጭቱን ወደ ሥራ የሚቀይር ትውልድ ከመፍጠር ግን ማስቆም አልቻለችም።
ይህ ትውልድ የአባቶቹን ተረቶች እና የቁጭት እንጉርጉሮዎች ብቻ ወርሶ ዝም ማለት አልቻለምና ድፍረት የተሞላበት ውሳኔ ወሰነ። ለዓባይ ዘላለማዊ ማደሪያ ሊያዘጋጅ ቆርጦ ወደ ሥራ ገባ። በርካቶች ይህ ሙከራ ከፉከራ አያልፍም ብለው ቢሳለቁም የሕዳሴ ትውልድ ግን የዓባይን ማደሪያ ለማበጀት ተማከረና ዓባይን ዋናው ማደሪያህን እስከማዘጋጅልህ ድረስ ለጊዜው ወዲህ ዞር በል ቢለው ዓባይም ምንተዳዬ ብሎ ታዘዘ። ያኔ ነበር ምንም አያመጡም ያሉት ሁሉ የህልም ሩጫቸውን መሮጥ የጀመሩት። ቁጭት የወለደውን ውሳኔ የሚያቆመው ምድራዊ ኃይል የለምና ሕዳሴን ማቆም የሚችል አልተገኘም።
ቁጭት የወለደው ሕዳሴም በኢትዮጵያ ልጆች እንባ፣ ላብ እና ደም ተገንብቶ ጉባ ላይ ተሞሸረ። ዓባይም ድሮውንም ባይተዋር አድርጋችሁኝ እንጂ የሰው ቤትማ የሰው ነው ብሎ ጉባ ላይ አረፍ አለ።
የሕዳሴ ጀግኖች አሁን የምን ውኃ መጠማት ነው እያሉ ተረቱን ማማት ጀምረዋል። ዓባይም እኔ እያለሁን እናንተን ከሚጠማ እኔን ይጥማኝ ብሎ ኩልል ብሎ እየፈሰሰ ነው። ደግነቱ ዓባይም ኢትዮጵያውያንም ንፉግ አይደሉምና ከግብፅ ጋር የነበረውን የዓባይን ቃልኪዳንም አላፈረሱም። ኢትዮጵያ እኔ ከጠጣሁ ሌለው ቢጠማ ምን አገባኝ እንዳማትለው ሁሉ የደጇ በረከት የሆነው ዓባይም ለሁሉም እበቃለሁ ብሎ ሸክሙን አራግፎ ወደ ግብፅ መጓዙን ቀጥሏል።
ይህ ዘመን የዓባይን ልጅ ውኃ ጠማው ለሚለው ተረት ምላሽ የተገኘበት ዘመን ነው። ተረቱን መልሶ ከማስተጋባት “የዓባይን ልጅ ለምን ውኃ ጠማው?” ብሎ የጠየቀው የመደመር ትውልድ “ዓባይን ስላላሳደርን ነው” የሚል ምላሽ አግኝቶ ማደሪያውንም አዘጋጅቶ የከፍታ ጉዞውን ጀምሯል።
የዓባይ ቁጭት የአንድ ወንዝ ብቻ ቁጭት እንዳልሆነ ሁሉ የዓባይ ልማትም የኢትዮጵያ ዳግም ትንሣኤ ማብሰሪያ ነው።
የመደመር መንግሥት በገፅ 41 ላይ “የዓባይን ልጅ ለምን ውኃ ጠማው?” ብሎ ይጠቀይቅና ኢትዮጵያ በሀብት ሆነ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የታደለች ብትሆንም ይህን ስጦታዋን ስላልተጠቀመች ግን ውኃ ላይ ተቀምጣ መጠማቷን ይገልጻል።
የመደመር መንግሥት ይቀጥልና፣ “ኢትዮጵያ ከስጦታዎች ይህ አጠራት የምትባል አይደለችም። እነዚህን የተፈጥሮ ችሮታዎች ተጠቅመን ማደግ እንዳንችል ብዙ ተግዳሮቶችን በታሪካችን አሳልፈናል። በሆኑ ዘመናት ብቅ ያሉትን የፈጠራ ፍንጮችም፤ ፈጥነን ወደ ዘላቂ ልማት አልቀየርናቸውም። ያለንን ጸጋም አዳዲስ ሀብት ለመፍጠር አልተጠቀምንም። እነዚህ ተግዳሮቶች አንዱ ለአንዱ መነሻ ምከንያት እየሆነ፤ ዛሬ ካለንበት የድህነት ደረጃ ላይ እንገኛለን። የመከራ አዙሪትና የሥልጣኔ ሾተላይ አለብን።” ይላል።
ደምስሶ መቅዳት እና አፍርሶ መሥራት ሌላኛው ኢትዮጵያን ወደ ኋላ ያስቀራት ጉዳይ እንደሆነ መጽሐፉ በግልፅ አስቀምጦታል። ትላንት የተሠሩት ላይ እየደመሩ ከመሄድ ሁሉም የራሱን እየጀመረ ተከታዩ ደግሞ ያንን እያፈረሰ አዲስ ሲጀምር አንዱም ሳይፈጸም እዚህ ተደርሷል። በዚህም ሀብት እና ጉልበት ሲባክን ዓለምን ካስደነቀው የኢትዮጵያ ሥልጣኔም አንዳች ነገር ለትውልድ ሳይተላለፍ የኢትዮጵያ መገለጫ ድህነት ሆኖ ቆይቷል።
አረንጓዴ መሬት ይዞ መራብ፣ ውኃ ላይ ተቀምጦ መጠማት ማለት ይኸ ነው። የመደመር ትውልድ ይህን አዙሪት ባለበት በማቆም ወደ ፊት ለመዝለል ቆርጦ ተነስቷል። ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የደምስሶ መቅዳት እና የአፍርሶ መገንባት አዙሪት የተሰበረበት የኢትዮጵያ ትንሣኤ ማብሰሪያ ነው። ሕዳሴ ከቁጭት አስከ ጥናት፣ ከጅማሮ እስከ ፍጻሜው የትውልድ ቅብብሎሽ ነውና እንዲህም እየደመሩ ማሳደግ ይቻላል የሚል መልዕክት የሚያስተላለፍ ነው።
አሁን ተረቱን ማማት ሳይሆን ምላሹንም በሕዳሴ አግኝተንለታል። ሕዳሴ ላይ በተበሰሩ ፕሮጀክቶች ደግሞ ተረቱን እና ቁጭቱን መበቀል ተጀምሯል።
በለሚ ታደሰ