የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሕዝብ እና የመንግሥት ትብብር ወሳኝ ነው ሲሉ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዮት የመካከለኛው ምስራቅ፣ እስያና ፓሲፊክ ጉዳዮች ዳይሬክተር አማረ ቀናው (ዶ/ር) ገለጹ።
ዶ/ር አማረ ከኢቲቪ ዜና ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ የባሕር በር ጥያቄ ብሔራዊ አጀንዳችን አድርገን እየተንቀሳቀስንበት ያለ ቁልፍ ጉዳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣቷ ኢኮኖሚዋ በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ እና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዳትሆን በማድረግ ለበርካታ ዓመታት ሲጎዳት መቆየቱን አንስተዋል።
በዚህም የባሕር በር ካጣችበት ጊዜ አንስቶ የኢኮኖሚ ዕድገቷ በየዓመቱ ከ20 እስከ 30 በመቶ በሚደርስ ምጣኔ ስለመገታቱም ነው የገለጹት።

በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ 12 የወደብ መዳረሻዎች ኢትዮጵያ እስከአሁን በአንዱ ላይ ብቻ ተወስና ለመቆየት መገደዷን አንስተው፤ ለኪራዩም በዓመት 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደምታወጣ ጠቅሰዋል።
በዚህም ከአጠቃላይ የሀገራችን ጂዲፒ የሚገኘው ትርፍ ለኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ልማት መዋል ሲገባው ለወደብ ኪራይ ክፍያ እየባከነ ስለመሆኑም ነው ያመላከቱት።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ያላት ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ የባለቤትነት መብት በዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ የተደገፈ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሀገራችን የባሕር በር ለማግኘት የጀመረችውን እንቅስቃሴ ቀጣናዊ ትብብርን በሚያጎለብት አግባብ አጠናክራ እንደምትቀጥልበት ተናግረዋል።
በሐይማኖት ከበደ
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #seaaccess #redse