Search

የሰለጠኑትን ስናልም መሰልጠኛውን የረሳነው ዕደጥበባችን

ዓርብ ታኅሣሥ 03, 2018 61

ጃፓን እንደምን ሰለጠነች ከሚለው የማደግ ጉጉት ጀምሮ በየሀገራቱ የነበሩ የልምድ ልውውጥ ሂደቶች ኢትዮጵያን እንደአደጉት ሀገራት የማድረግ መሻት መሆኑን ማን ያጣዋል? በተለይ ከንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያን ዘመናዊት ሀገር የማድረጉ ፍላጎት ቅኝቱ አውሮፓዊ መንገድን የመከተል ፍላጎት የነበረው ይመስላል። በኋላ የሶሻሊስት ሀገራትን ተሞክሮ ያየው የደርግ መንግሥትም እንደ ሩስያ የመሆን ህልሙ ኢትዮጵያን ለማሳደግ ነበር።

ከ1983 ወዲህ “እንደ ኮሪያ ሁሉ የረገጡትን ድንጋይ ረግጠን ቻይና ባለፈችበት መንገድ ተጉዘን” የሚለውም ምርጫ የመሆን ፍላጎት እንጂ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ምን አላት? ብሎ ለመጠየቅ እድሉን ያገኘ ትውልድ አልነበረም።

ከጃፓን በደቡብ ኮሪያ አድርገን እስከ ቻይና እና ሩስያ አልፈን ደግሞ ከአውሮፓም ከአሜሪካም ያለፉበት መንገድ ቢያስቀናን የማደጊያ ታክቲካችን እንደእነሱ መሆንን መመረጥ እንጂ ያለነን ለመመልከት የጎደለንን ለመዋስ የፈቀደ ባለመሆኑ ዘመናትን ስንገነባ ስናፈርስ ለመጓዝ ተገደናል።

ታዲያ እንደአደጉት ለማደግ መሻታችን ልክ ቢሆንም ሁሉን ከውጭ አምጥተን ያልንበት መንገድ መዳረሻችንን አላሳየንም። እናም እዚህ ላይ ኢትዮጵያ የነበራትን ሁሉ ባህላዊ እና ኋላቀር እያለች የውጭው ብቻ ጥሩ እየመሰላት መጓዟ ብዙ መንገድ አልወሰዳትም።

ታዲያ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ አሊያም ቻይና ለእድገታቸው ቁልፍ የሆኑላቸውን ጥንታዊ እና ባህላዊ የእደ ጥበብ ዕቃዎቻቸውን ከዘመናዊ ኢንዱስትሪ ጋር በማናበብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ ወደ ሆኑ ምርቶች ያሳደጉበትን ጥበብ ስለምን አልቀሰምንም የሚል የረባ ምላሽ የሚያገኝ አይመስልም

እውነታው ግን ደቡብ ኮሪያ ባህላዊ እደ ጥበቧን ወደ ዘመናዊ ዲዛይን እና ኢንዱስትሪ በመቀየር ለዓለም ገበያ እስከ ማቅረብ ደርሳለች፡፡ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ የነበረውን የኢኮኖሚ ዕድገቷን ተከትሎ እደጥበቧን በማዘመን ለሙያተኞቿ ተገቢውን ክብር ሰጥታለች።

መንግሥት የኮሪያ የእጅ ሥራ እና ዲዛይን ፋውንዴሽን ማኅበርን (KCDF) በማቋቋም የኮሪያን ባህላዊ የእደ ጥበብ መሣሪያዎች እንዲያዘምኑ አድርጓል። ፋውንዴሽኑ ለእደ ጥበብ ባለሙያዎች ድጎማ፣ የንድፍ ምክክር እና የግብይት ድጋፍ በመስጠት ከዘመናዊ ገበያዎች ጋር እንዲላመዱ ይረዳቸዋል።

ስልቱ የኮሪያ ባህላዊ የእደ ጥበብ ሥራዎችን ከዘመናዊ ምርቶች ጋር በማዋሃድ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ መቀላቀል ሲሆን፣ ይህም ምርቶቹም በንድፎቻቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሸማቾችን ቀልብ እንዲገዙ ረድቷል። ባህላዊ የእደ-ጥበብ ሥራዎቿን ከጠንካራ የቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ዲዛይን ዘርፎቿ ጋር በተሳካ ሁኔታ አዋህዳለች።

በመንግሥት ድጋፍ የተቋቋመው "K-Crafts" ባህላዊ የእደ ጥበብ ሥራዎችን በከፍተኛ ጥራት በማምረት "ሃሊዩ" (የኮሪያ ሞገድ) የፈጠረ ሲሆን፣ የኮሪያ የእደ ጥበብ ውጤቶች ዓለም አቀፋዊ ተወዳጅነት እንዲያገኙ አድርጓል።

የጃፓን የዘመናዊነት ሂደት የጀመረው በሜጂ ተሃድሶ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ሲሆን፣ ባህልን ከቴክኒካዊ ችሎታ እና ከብሔራዊ ማንነት ጋር በመዋሃድ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል። የዘመናዊ ኢንዱስትሪ ዕድገት በእደ ጥበቧ ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ አስቀድማ ተረድታለች። ነባሮቹን የእደ ጥበብ ሙያዎች ለመጠበቅም መንግሥት የነባር ብሔራዊ ሀብት ሥርዓትን ያቋቋመ ሲሆን፣ ልዩ ችሎታ ላላቸው የእደ ጥበብ ባለሞያዎች የክብር ማዕረግ እና የድጎማ ሥርዓት አዘጋጅቷል። ይህ ሥርዓትም የጃፓን ባህል እና ነባር ክህሎት በትውልዶች ውስጥ እንዲቀጥል አስችሏል፡፡

እንደ የእንጨት፣ የወረቀት ስክሪኖች፣ ሴራሚክስ እና ጨርቃ ጨርቅ ያሉ ጥንታዊ የእደ ጥበብ ሥራዎች ከዘመናዊው የጃፓን ምህንድስና እና የውበት ሥራ ጋር በጥልቀት እንዲዋሃዱ ተደርገዋል። ይህ ትኩረት ወደር በሌለው ጥራት እና በጥልቅ ክህሎት የተሠሩ የጃፓን የእደ ጥበብ ውጤቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ፕሪሚየም ዋጋን እንዲገኙ ያደረጋቸው ሲሆን፣ ይህም የጃፓን የእደ ጥበብ ውጤቶች የቅንጦት ዕቃ ፈላጊዎችን ቀልብ እንዲገዛ አድርጎታል።

የእሴት ሰንሰለትን በመፍጠር፣ የመንግሥት ድጋፍ እና ውበትን ማላመድ ሁለቱ ሀገራት የእደ ጥበብ ሥራዎቻቸውን ያሳደጉበት መንገድ ነው፡፡ ለጥንታዊ የእደ ጥበብ ሥራዎቻቸው በሰጡት ትኩረት መሰረት ሆኗቸውም ዛሬ የዓለም የኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃን ሊቆጣጠሩ ችለዋል፡፡

ሀብቷን ያልተጠቀመችበት ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ዘመናዊ ኢንዱስትሪ ሳይመጣ በፊት በሸክላ፣ በቆዳ፣ በብረታ በረት፣ በጨርቃ ጨርቅ እና በሌሎች የእደ ጥበብ ክህሎታቸው ያገለገሏት ምርጥ ባለሙያዎች አሏት፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ግን ተገቢውን ክብር ሳያገኙ ኖረዋል፡፡ ሸማኔ የሠራውን እየለበሱ ሸማኔውን "ቁጢት በጣሽ" የሚሉ፣ በሸክላ እየበሉ ሸክላ ሠሪውን የሚያንቋሽሹ፣ ቆዳ ሠሪ በሠራው ቁርበት እየተኙ ሠሪውን "ፋቂ" የሚሉ ሰዎች ኢትዮጵያን ዋጋ አስከፍለዋታል፡፡

ይህ ሥራን እና ሠራተኛን የማንቋሸሽ አባዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራን ዝቅ ብሎ የመሥራት ባህል እንዳይኖር አድርጎታል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቀው ይህ መጥፎ ልማድ ኢትዮጵያ ከእደ ጥበብ ዘርፍ ልታገኘው የሚገባትን እንዳታገኝ ከማድረጉም አልፎ ሥራን የመናቅ መጥፎ ልማድ እንዲዳብር መንገድ ከፍቷል፡፡ በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ መሰረትም በክህሎት የበቃ የሰው ኃይል እጥረት ገጥሟት ኖሯል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በመደመር መንግሥት መጽሐፋቸው ለሥራ እና ሠራተኛ የተሰጠው ክብር ዝቅተኛ መሆኑን እና ይህ ልማድ ኢትዮጵያን ዋጋ እንዳስከፈላት ጠቅሰዋል፡፡ የመደመር መንግሥት ገጽ 66 ላይ፣ “በነገሥታቱ ዘመን ሰውን ባሪያ እና ጌታ ብለው ሲፈርጁ ሥራን ደግሞ ከብር ያለው እና የተናቀ ብለው ከፍለውታል። የዘመኑ ልሂቃንም የሚቃወሙት ሳይሆን በዚያ ሥርዓት ውስጥ ዕድገታቸውን ማመቻቸት እና ለክፍፍሉ ሐሳብ አፍላቂዎች ሆነዋል፡፡ በሽመና ሥራ የተሠማሩት ቁጢት በጣሽ ተባሉ፡፡ የብረታ ብረት ባለሞያዎች ቀጥቃጭ የሚል የንቀት ስም ተሰጣቸው። ገበሬው አፈርገፊ ተባለ። ነጋዴው መጫኛ ነካሽ ተብሎ በመሰደቡ የንግድ ባህል በማኅበረሰብ ውስጥ እንዳይጎለብት አድርጓል” ይላል።

ይህ ደግሞ ከእኛ እኩል በእደ ጥበብ እና በሌሎች ሥራዎች የታወቁ እንደኮሪያ ያሉ የሩቅ ምሥራቅ ሀገራት ዘርፉን በማሻሻላቸው እና የማኅበረሰባቸውን ባህል በመቀየራቸው ምርቶቻቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ እንደሆኑ በመጽሐፉ ላይ ተጠቅሷል፡፡

ኢትዮጵያ ለጦር እና ጦረኝነት የምትሰጠውን ዋጋ ለሙያ ባለመስጠቷ ቀድማ ተነስታ ከሌሎች ወደኋላ መቅረቷም በመጽሐፉ ገጽ 67 ላይ በደንብ ተብራርቷል፡፡

በለሚ ታደሰ