ኢትዮጵያ ለእያንዳንዱ ዜጋ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ እምነት የሚጣልበት እና ሁሉን አቀፍ የዲጂታል አገልግሎቶችን ማግኘት የሚያስችል ብሔራዊ መታወቂያ እየሰጠች ትገኛለች፡፡
ለሁሉም አገልግሎቶች አስፈላጊ የሆነውን ብሔራዊ መታወቂያ እስካሁን ከ29 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መውሰዳቸውን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የብሔራዊ መታወቂያ አስተባባሪ አቶ ደጄኔ ገብሬ ጠቁመዋል፡፡
አቶ ደጄኔ ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት የብሔራዊ መታወቂያ ተመዝጋቢዎችን ቁጥር 90 ሚሊዮን ለማድረስ እየተሰራ ነው፡፡
ይህን ለማሳካትም በሁሉም ክልሎች ባሉ ወረዳዎች እድሜያቸው ከአምስት ዓመት ጀምሮ ያሉ ዜጎች እንዲመዘገቡ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ፋይዳ የሚል ስያሜ ያለው የኢትዮጵያ ዲጅታል መታወቂያ ቴክኖሎጅውን በማስፋፋት ለዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎቶችን ለመስጠት እንደሚያግዝም አቶ ደጄኔ ተናግረዋል፡፡
ዲጂታል ቴክኖሎጅው ደግሞ የመደመር መንግስት እሳቤ የሆኑትን መፍጠር፣ መፍጠን እና መዝለልን ከግብ ለማድረስ የሚረዳ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በተለመደው አካሄድ ወደ ከፍታ መሻገር አይቻልም ያሉት አስተባባሪው፤ ያሉን ነገሮች ላይ ፈጠራ በማከል በፈጣን ጉዞ ሀገራችንን ማሳደግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
እንደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ያሉ ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀምም አላስፈላጊ ሂደቶችን በመዝለል፤ አለም የደረሰበት ደረጃ መድረስ እና የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ማረጋገጥ እንደሚቻል አክለዋል፡፡
የአንድ መሶብ አገልግሎትን በሁሉም ክልሎች በማስፋፋት ከ40 በላይ ተቋማት በአንድ ቦታ አገልግሎቶችን መስጠት መጀመራቸውም ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እንደሚያግዝ አንስተዋል፡፡
የተገልጋዮችን እንግልት ለመቀነስም 800 አይነት የመንግስት አገልግሎቶች ወደ ዲጅታል መቀየራቸውን ገልፀዋል፡፡
ዜጎች እስከ መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የባንክ ሂሳባቸውን ከፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ ጋር እንዲያስተሳስሩ ብሔራዊ ባንክ ከሰሞኑን ጥሪ ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡
በየተመኙሽ አያሌው
#Ebc #Ebcdotstream #Ethiopia #Fayda #DigitalEthiopia