Search

ኢትዮጵያ ለዘመናት ባስተዳደረችው ባህር ላይ የበይ ተመልካች መሆን የለባትም

እሑድ ታኅሣሥ 05, 2018 172

ቀይ ባሕር የሕንድ ውቅያኖስን እና ሜዲትራኒያን ባሕርን በማገናኘት በተለይም በዓለም ዙሪያ ተፈላጊ የሆነውን ነዳጅ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከባሕረ ሰላጤው አገራት ለማጓጓዝ አጭር መንገድ በመሆኑ በዓለም ንግድ እና ፖለቲካ ላይ ወሳኝ ቦታ አለው።

በቻይና እና በአውሮፓ መካከል ከሚደረገው የንግድ ልውውጥ ውስጥ ሁለት ሶስተኛው የሚያልፈው በዚሁ ባህር ነው።

ቁልፍ መረጃ የሚተላለፍባቸው የዓለም የኮሙዩኒኬሽን መስመሮች በዚህ ባህር ውስጥ ጥልቅ መሬቱን ተንተርሰውም ይገኛሉ።

ግዙፍ የባህር ኃይል ያላቸው የዓለም ሀገራት ደህንነታቸው ተጠብቆ በቀይ ባህር ቀዝፈው ወደ ሞቃታማው የህንድ ውቅያኖስ የሚያልፉበትም መስመር ነው።

ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር ቆይታ ያደረጉት የዓለም አቀፍ ውኃ ህግ ባለሙያው ከበደ ገርባ (ዶ/ር)፤ ከቀይ ባህር በጥቂት ርቀት የተቀመጠችው ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ ለዘመናት ባስተዳደረችው ባህር የበይ ተመልካች ሆና ተቀምጣለች ብለዋል።

በራስ ደጃፍ የበይ ተመልካችነት በዚህ ተለዋዋጭ የዓለም ሁኔታ ብዙ የሚያራምድ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል።

የመደመር መንግሥት የባህር በር ጥያቄን የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ እና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ አካል አድርጎ እንደሚመለከት ገልጸዋል።

ከ120 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት እና በቀጠናው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ያለችው ኢትዮጵያ የቀይ ባህር መስመር ላይ የሯሷ የሆነ ተመጣጣኝ መድረክ ያስፈልጋታል ሲሉ ጠቁመዋል። 

ይህ ሀሳብ ለብዙ ዓመታት የነበረ የኢትዮጵያ ጥያቄ ነው የሚሉት ባለሙያው፤ ይህን ጉዳይ የአንድ ፓርቲ አጀንዳ አድርጎ መመልከት አይገባም ብለዋል።

የሀገራችን ብሔራዊ ደህንነት በመሆኑም ሁሉም አካል መጠየቅ ይገባዋል ሲሉ አክለዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት የነበረች በመሆኗ ቀይ ባህር ላይ ታሪካዊ መብት እንዳላትና በዓለም አቀፍ ህግም ጉዳዩ በፍትሀዊነት እንደሚታይ አንስተዋል።

የባህር በር ለኢትዮጵያ ወደቀደመ ገናናነት ለመመለስ የብሩህ ተስፋ ምልክትም ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በሜሮን ንብረት

#Ebc #EBCDOTSTREAM #Ethiopia #redsea #nationalinterest