Search

የሁሉም የስፖርት ውርርድ ድርጅቶች ፈቃድ ተሰረዘ

ሰኞ ታኅሣሥ 06, 2018 121

በኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ፈቃድ ተሰጥቷቸው ሲሰሩ የቆዩ የሁሉም የስፖርት ውርርድ ድርጅቶች የሥራ ፈቃድ መሰረዙን አገልግሎቱ አስታወቀ፡፡
የሁሉም የስፖርት ውርርድ ድርጅቶች የሥራ ፈቃዶች በዛሬ ጀምሮ መሰረዛቸውን ነው የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ያስታወቀው ፡፡
የፈቃድ ስረዛው በውርርድ እና በፋይናንስ ዘርፉ ላይ በተካሄደ ሀገር አቀፍ ጥልቅ ግምገማ ላይ ተመስርቶ የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር የተወሰደ እርምጃ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ውሳኔው በሥራ ላይ ባሉትና ቀደም ሲል በይፋ በታገዱት በሁሉም የውርርድ ድርጅቶች በእኩልነት ተፈጻሚ የሚሆን ነው፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሂደት ላይ ያለው ምርመራ በዘርፉ ውስጥ የተንሰራፋ ሕገ ወጥ አሰራር፣ የፈቃድ ውል ጥሰት እና ለብሔራዊ ደህንነት ስጋት የሚሆኑ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሮች እንዳሉ በግልጽ አመላክቷል።
አገልግሎቱ ለሚመለከታቸው አካላት መመሪያ አስተለልፏል፡፡ በዚህም መሰረት፡-
1. ለስፖርት ውርርድ ድርጅቶች እና ሲስተም ኦፕሬተሮች/አቅራቢዎች
ከታሕሳስ 06 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአካል፣ በዲጂታል ወይም በሌላ መንገድ የሚካሄድ ማንኛውንም የውርርድ ሥራ ወዲያውኑ ማቋረጥ ይጠበቅባቸዋል።
ሁሉም የገንዘብ ማስገቢያ መንገዶች (Deposit Gateways) አገልግሎት መስጠት ማቆም አለባቸው። አዲስ ውርርድ መቀበል ፈጽሞ አይቻልም።
ሁሉም የሰርቨር መረጃዎችን፣ የፋይናንስ መዝገቦችን እና የተጠቃሚ መረጃዎችን በጥብቅ ጠብቀው የማቆየት ግዴታ አለባቸው። ማስረጃን ማጥፋት፣ መቀየር ወይም ማሸሽ በወንጀል ሕጉ መሰረት ያስቀጣል።
2. ለፋይናንስ ተቋማት (ባንኮች፣ ፔይመንት ኢንስቱርመንት ኢሹወርስ እና ፔይመንት ሲስተም ኦፕሬተሮች)
ከታሕሳስ 06 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ፣ የሁሉም የውርርድ ድርጅቶች የሥራ ፈቃድ በመሰረዙ፣ በተቋማቱ በኩል የውርርድ ድርጅቶቹ የሽያጭ እንቅስቃሴ እንዳያከናውኑ እንዲያደርጉ ጥብቅ መመሪያ ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ይህን ውሳኔ ከሁሉም የመንግሥት ተቋማት ጋር በመተባበር በጥብቅ የሚከታተል መሆኑን አስታውቆ፣ መመሪያውን የሚጥስ ማንኛውም አካል በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆን ገልጿል።