"የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች" በሚል መሪ ቃል በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች ላይ ተሳታፊ የነበሩ ዜጎች በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም በብሔራዊ ጥቅም ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 በተደረገ ወቅታዊ ውይይት፤ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ምክትል ኃላፊና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ዓለምፀሐይ ሽፈራው እንደተናገሩት፣ በመድረኮቹ የመደመር መንግሥት ስኬቶችና ክፍተቶች በተገቢው መንገድ ተነስተዋል።
በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን መተማመን በማጠናከር፣ የመረጃ ጥራት መፍጠርና የዴሞክራሲ ሥርዓትን በማጎልበት ረገድ መድረኮቹ ስኬታማ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የጉባ ብስራት ፕሮጀክቶች ፍትሐዊ የሀብት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡና የዜጎችን የባለቤትነት ስሜት ከፍ የሚያደርጉ መሆናቸውን በውይይቶቹ መነሳቱን ምክትል ኃላፊዋ አስታውቀዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሕዝባዊ ውይይቶቹ ዜጎች የጋራ ስኬታቸውን በመገንዘብ ክፍተቶችን ለማረም እንዲተባበሩ ጉልበት የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።
ውይይቶቹ የወል ትርክትን ለመገንባት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራቸውም አመላክተዋል።
በሕዝባዊ የውይይት መድረኮቹ ዜጎች ከአስተያየትና ጥያቄ ባለፈ፣ በኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ውስጥ የበኩላቸውን ድርሻ በሚወጡባቸው መንገዶች ላይ መግባባት መቻሉ ተገልጿል።
በቤተልሔም ገረመው