ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የሚረዳ መሠረተ ልማትን ማስፋፋት እና ለዚሁ ሥራ የሚያግዝ የኃይል ትስስርን መፍጠር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።
በተጠናቀቀው የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ስትራቴጂም ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው የተለያዩ የቴሌኮም ዘርፍ ሥራዎች ተከናውነዋል።
በዚህም አጠቃላይ የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 97 ሚሊዮን ሲደርስ፤ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ደግሞ ወደ 57 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ ይፋ በተደረገበት ወቅት ገልጸዋል።
በመላ ሀገሪቱ በተደረገው መጠነ-ሰፊ የማስፋፊያ ሥራም ከ13 ሺህ በላይ የሞባይል ጣቢያዎች እና በርካታ የፋይበር መሠረተ ልማቶች መገንባታቸውን ነው ያስረዱት።
በተከናወነው የማስፋፊያ ሥራ ከአንድ ሺህ ሠላሳ በላይ ከተሞች የ4ጂ አገልግሎት እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፣ ይህም የ4ጂ ተደራሽነት በኢትዮጵያ ወደ 76 በመቶ እንዲያድግ ማስቻሉን አብራርተዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በዓለም የዲጂታል መድረክ ላይ የራሷን ዐሻራ እንድታሳርፍ ያስቻሏት ሥራዎች መከናወናቸውንና በአሁኑ ወቅት 27 ከተሞች የ5ጂ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የሞባይል ገንዘብ ልውውጥ በሚገርም ፍጥነት ማደጉን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤ በአሁኑ ወቅት ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) ውስጥ 82 በመቶ የሚሆነው የፋይናንስ ልውውጥ በዲጂታል ፕላትፎርሞች አማካኝነት እየተከናወነ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በቀጣይም የተጠናከረ የዲጂታላይዜሽን ሥራ እንደሚከናወን ጠቁመው፤ በ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ መሠረት የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ቁጥር 87 ሚሊዮን፣ የስማርት ስልክ ተደራሽነትን ደግሞ 85 በመቶ ለማድረስ መታቀዱን አመላክተዋል። ይህም በዘርፉ ለ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል ብለዋል።
የስማርት ስልክ ተደራሽነቱ በአሁኑ ወቅት 46 በመቶ መድረሱን የጠቀሱት ፍሬሕይወት ታምሩ፤ ይህንን ቁጥር በእጅጉ በማሳደግ የዜጎችን የዲጂታል ተጠቃሚነት ማጎልበት ላይ ሰፊ ትኩረት መሰጠቱንም አረጋግጠዋል።
በአፎሚያ ክበበው