የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ስታርት አፖችን የኢኮኖሚው ዋነኛ ሞተር በማድረግ፣ የፈጠራ ሥራዎች ወደ ስኬታማ ቢዝነስ እንዲለወጡና ወጣቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል መሠረት ጥሏል።
ስትራቴጂው ዜጋ ተኮርና ሁሉን አቀፍ የዲጂታል አሠራር እንዲሰፍን እንዲሁም የፈጠራ ሥራዎች እንዲበረታቱ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑንም ከኢቲቪ አዲስ ቀን መሰናዶ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የስታርት አፕ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሰላምይሁን አደፍርስ ገልጸዋል።
የስታርት አፖችን አቅም ይበልጥ ለማሳደግ የሚረዳ ስትራቴጂ መሆኑንም ጠቁመው፤ ለአዳዲስ እና በቴክኖሎጂ ላይ ለተመሠረቱ የፈጠራ ሥራዎች ቢዝነስ ስኬታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም አንስተዋል።
የንግድ ሥራዎች ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር ሲቀናጁ የሚኖራቸው ውጤት አመርቂ መሆኑን የጠቀሱት ሰላምይሁን አደፍርስ፤ ስትራቴጂው በፈጠራ የታጀበ ፈጣን የዲጂታል ሽግግር ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
ከዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተገኙ ተሞክሮዎችን መነሻ በማድረግ፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ወጣቶች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ወደ ተግባራዊ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲለውጡና የውጭ ምንዛሬ ግኝትን እንዲያሳድጉ ትልቅ ተስፋ መጣሉንም ገልጸዋል።
ስትራቴጂው ወጣቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ መንገድ ከመክፈቱም ባለፈ፣ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ መሠረት በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ እንደሚያስችል አስረድተዋል።
በወጣቶች የሚመሩ የፈጠራ ሥራዎች ወደ ንግድ ተለውጠው ለኢኮኖሚው ዕድገት የላቀ ድርሻ እንዲያበረክቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በትኩረት እንደሚሠራ ሰላምይሁን አደፍርስ አመላክተዋል።
በሜሮን ንብረት