Search

ለአርሶ አደሮች ጥቅም የሚሰጠው - ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030

ረቡዕ ታኅሣሥ 15, 2018 456

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ከያዛቸው ዋና ዋና ግቦች መካከል የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን አንዱ ነው።

የአርሶ አደሩን የዕለት ተዕለት ተግባር ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር በማጣመር ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የታሰበው ይህ ስትራቴጂ፣ ከሚያበረክታቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የታገዘ የምክር አገልግሎት

ለሺህ ዘመናት የዘለቀው ባህላዊ የግብርና ሥራ በሰው ኃይል ላይ ብቻ የተመሰረተ በመሆኑ፣ አርሶ አደሩ ወቅታዊ መረጃ የሚያገኝበት ዕድል አነስተኛ ነበር።

ይህንን ክፍተት ለመሙላት "የዲጂታል ግብርና የምክር አገልግሎት (DAAS)" የተሰኘ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚታገዝ ዘዴ ሥራ ላይ ውሏል።

ይህ ቴክኖሎጂ አርሶ አደሩ ስለ አየር ሁኔታ ትንበያ፣ ስለ ሰብል ዝግጅት እና ስለ ማዳበሪያ አጠቃቀም መረጃዎችን በሞባይል ስልኩ (በጽሁፍ ወይም በድምፅ) በፍጥነት እንዲያገኝ ያስችላል።

በዚህም አርሶ አደሮች የአየር ሁኔታ መረጃን አስቀድመው በማወቅ፣ በድንገተኛ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሰብል ላይ ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን መከላከል ይችላሉ።

በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የታገዘ የበሽታ መከላከል


አርሶ አደሮች አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም የሰብል በሽታዎችን በቀላሉ መለየት ይችላሉ። ለምሳሌ የቡና ወይም የጥራጥሬ ሰብል በሽታዎችን በስልክ ፎቶ በማንሳት ብቻ መፍትሔ የሚያገኙበት አሰራር ተዘርግቷል።

ይህም በሽታው ሳይሰራጭ በፍጥነት እርምጃ ለመውሰድ እና የምርት ብክነትን ለመቀነስ ይረዳል።

ቀጥተኛ የገበያ ትስስር መፍጠር

አርሶ አደሩ በተለያዩ የሀገሪቱ ገበያዎች ያለውን የዋጋ መረጃ በቀጥታ በስልኩ እንዲያገኝ በማድረግ፣ ምርቱን የት እና መቼ መሸጥ እንዳለበት የተሻለ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ያግዘዋል። ይህም አርሶ አደሩን ከደላላ ብዝበዛ በመጠበቅ የልፋቱን ተገቢ ዋጋ እንዲያገኝ ያስችለዋል።

ዳታ ላይ የተመረኮዘ ምርታማነት

አርሶ አደሩ እንደ አፈሩ ዓይነት ምን ዓይነት ማዳበሪያ እና ዘር መጠቀም እንዳለበት ሳይንሳዊ ምክር እንዲያገኝ ይደረጋል።

ይህ ትክክለኛ መንገድን የተከተለ ግብርና (Precision Farming) አላስፈላጊ የግብዓት ብክነትን ከመቀነሱም ባለፈ፣ በሔክታር የሚገኘውን ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ያደርጋል።

የዲጂታል ፋይናንስ እና የመታወቂያ አገልግሎት

በስትራቴጂው መሠረት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ከአርሶ አደሩ የእርሻና የምርት ታሪክ ጋር በመቀናጀት፣ አርሶ አደሮች በቀላሉ የባንክ ብድር እና የኢንሹራንስ አገልግሎት እንዲያገኙ መንገድ ይከፍታል።

በአጠቃላይ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ግብርናውን ከልማዳዊ አሠራር በማውጣት፣ በቴክኖሎጂ ወደሚመራ ዘመናዊ የግብርና ዘዴ የሚቀይር ድልድይ ሆኖ ያገለግላል።

 

በዋሲሁን ተስፋዬ