Search

80 ዓመታትን በከፍታ

ረቡዕ ታኅሣሥ 15, 2018 563

ተቋም ትውልድን ተሻግሮ የሀገር ምልክት ሲሆን ምን ይመስላል ቢሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብሎ ለመመለስ ጊዜ አይፈጅም፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፓን አፍሪካ ቀለም፣ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ኩራት ነው፡፡ በአፍሪካ ግንባር ቀደም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ ተወዳዳሪ ነው፡፡ በደኅንነቱ ብዙዎች የሚመርጡት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በከፍታው ላይ ለመቆየት እጅግ ከባድ ፈተናዎችን አልፏል፡፡ ሊወዳደሩት ያልቻሉት ሊያወርዱት ብዙ ጊዜ ሞክረውት ያልሆነላቸው ጽኑ መሰረት ስላለው ነው፡፡

አየር መንገዱ የመጀመሪያ በረራውን ካደረገባት ዳግላስ DC-3 በአፍሪካ የመጀመሪያው እስከሆነው ኤርባስ A350-1000 የመጣበት መንገድ ሲፈተሸ ምን ይመስላል?

እንዴትስ ፀንቶ ያለፉትን 80 ዓመታት በስኬት ጎዳና መጣ?

ማዲባ ጥቁር አብራሪ አይተው የተደነቁበት እና ከራሳቸው ጋር የተሟገቱበት የኢትዮጵያ አየር መንገድን በወፍ በረር እንቃኛለን፡፡

አየር መንገዱ በላቀ አገልግሎቱ የአፍሪካ ግንባር ቀደም አየር መንገድ በመባል እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደጋጋሚ ተሸልሟል፡፡ አስተማማኝነቱ፣ ደኅንነቱ እና የላቀ የደንበኞች አገልግሎቱ በአፍሪካ ግንባር ቀደም፣ በዓለም ደግሞ ብቁ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል አስችለውታል።

ታኅሳስ 12 ቀን 1938 . ተቋቁሞ መጋቢት 30 ቀን 1938 . በአሥመራ በኩል አድርጎ ወደ ካይሮ የመጀመሪያውን በረራ አደረገ፡፡ የመጀመሪያውን በረራ የጀመረባት አውሮፕላን ደግሞ እስከ 28 ተሳፋሪዎችን መያዝ የምትችለው ዳግላስ (Douglas C-47 Skytrain) ነበረች፡፡

ከአሜሪካው ትራንስ ወርልድ አየር መንገድ ጋር በመተባበር የካይሮ በረራውን በሳምንት አንዴ ቀጥሎ ወደ ጅቡቲ እና የመን እንዲሁም የሀገር ውስጥ በረራ ወደ ጅማ ቀጠለ፡፡

በዓመቱም መዳረሻውን በማስፋት ወደ ናይሮቢ፣ ፖርት ሱዳን እና ቦምቤይ መብረርጀመረ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ዓመት ለሃጅ ወደ መካ ለሚጓዙት ምእመናን የቻርተር አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

አየር መንገዱ 1950ዎቹ መዳረሻዎቹን ማስፋቱን የቀጠለ ሲሆን፣ እንደ ቦይንግ 720 ያሉ ትላልቅ አውሮፕላኖች ባለቤት ሆኗል። በአጭር ጊዜ ወደ ሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓ በረራ በመጀመር ዓለም አቀፍ አየር መንገድነቱን አረጋገጠ።

1970ዎቹ መገባደጃ ላይ ቦይንግ 727 እና 737 አውሮፕላኖችን በመግዛት ወደ ጄት ዘመን የገባ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ የጉዞ መስመሮችንም በእጅጉ ማስፋት ችሏል፡፡ በመቀጠልም የቦይንግ 757 እና ቦይንግ 767 አውሮፕላኖችን በመጨመር አድማስ ማካለሉን ቀጠለበት።

1983 እስከ 1987 . የነበረው ጊዜ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የኢኮኖሚ ፈተናዎች የነበሩበት ወቅት ነበር። ይሁን እንጂ በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባው አየር መንገዱ ወጀቡን ተቋቁሞ ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎቱን በቁርጠኝነት መስጠቱን ቀጠለ።

1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ እንደ ቦይንግ 777 ያሉ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በአፍሪካ አስተዋውቋል። እነዚህ አውሮፕላኖች ነዳጅ ቆጣቢ እና የመንገደኞችን ምቾት ያሻሻሉ ነበሩ። ሕዳር 2004 የግዙፉ የአየር መንገዶች ጥምረት ስታር አሊያንስ አባል በመሆን በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ተዓማኒነቱን አስፍቷል።

አገልግሎቱን ለማስፋት ባለው ቁርጠኝነትም በዘመናዊ አውሮፕላኖች ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አፍስሷል። ተፈትሸው ብቃታቸው የተረጋገጡ አውሮፕላኖችን በመግዛትም ከግንባር ቀደሞቹ መካከል ነው፡፡

የመጨረሻው የአቪየሽን ቴክኖሎጂ ውጤት የሆነው የተራቀቀ ኤሮዳይናሚክስ እና ውስጣዊ ገጽታዎች ያሉት Airbus A350-1000 አውሮፕላኖች ባለቤት ነው፡፡

የቦይንግ የመጨረሻ ቴክኖሎጂ የሆኑት 737 MAX አውሮፕላኖች ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የረጅም ጊዜ ቋሚ ደንበኛው ቦይንግ የአፍሪካ ዋና መሥሪያ ቤቱን በአዲስ አበባ እንዲከፍት ያስቻለ ተመራጭ አየር መንገድ ነው፡፡

80ኛ ዓመቱን ሲያከብር

አየር መንገዱ DC-3 እስከ እጅግ ዘመናዊው አውሮፕላን Airbus A350-1000 ያደረገው ጉዞ በአፍሪካ አቪየሽን ዘርፍ ብቁ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችለው ነው።

ዘርፉ ላይ ስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንት በማድረግ፣ የደህንነት መስፈርቶችን በማሟላት እና ለደንበኞች እርካታ ቅድሚያ በመስጠት አፍሪካን ከዓለም ጋር በማገናኘት ላይ ይገኛል፡፡

በየጊዜው ከሚለዋወጠው የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ፍላጎት ጋር በመናበብ በዓለም አቀፍ አቪዬሽን ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ ሆኖ ከደመና በላይ መቅዘፉን ቀጥሏል።

አየር መንገዱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2035 በዓመት 67 ሚሊዮን መንገደኞችን በማጓጓዝ 25 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ለማግኘት እየሠራ ይገኛል፡፡

የመጨረሻው ቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ አውሮፕላኖች ሁሉ ባለቤት የሆነው አየር መንገዱ፣ የ2035 ራዕዩን ለማሳካት ከ100 በላይ ተጨማሪ አውሮፕላኖችን አዝዞ አየተጠባበቀ ነው፡፡  

በአሁኑ ወቅትም ከ167 በላይ በሚሆኑት አውሮፕላኖቹ ከ145 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን እንደሚያካልል ከአየር መንገዱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

65 መዳረሻዎቹ አፍሪካ ውስጥ ናቸው፡፡ በአምስት አህጉራት ውስጥ 68 የጭነት መዳረሻዎችም አሉት፡፡ ወደ 22 የሀገር ውስጥ ከተሞችም በረራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

 

የፓን አፍሪካ አየር መንገድነቱን ለማጽናት እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ከፍ ለማድረግ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ በቢሾፍቱ ግዙፍ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡

ከጉባ ብሥራቶች አንዱ የሆነው የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ሲጠናቀቅ አየር መንገዱ ዓመታዊ የተሳፋሪዎቹን ቁጥር አሁን ከደረሰበት 19.1 ወደ 100 ሚሊዮን ያደርሳል፡፡

 

በለሚ ታደሰ