Search

በአዲሱ የትምህርት ሪፎርም በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በሥነ-ምግባር የታነጸ ዓለምን የሚመራ ትውልድ ለመገንባት እየተሠራ ነው - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

ቅዳሜ ሰኔ 20, 2018 47

ሀገራችን የጀመረችው አዲሱ የትምህርት ሪፎርም በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በፈጠራ የታነጸ፤ የነገውን ዓለም መረዳት እና መምራት የሚችል፣ ሀገራዊ ፍቅር እና የላቀ ሥነ-ምግባር ያለው ትውልድ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል።

አዲሱ ሥርዓተ-ትምህርት በብቃት ላይ የተመሠረተ፣ ሀገር በቀል ዕውቀትን እና ግብረ-ገብን ያካተተ እንዲሁም ትምህርትን ከምርት እና ተግባር ጋር ያሰናሰለ መሆኑን ቻንስለሩ በንግግራቸው አንስተዋል።

በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ከታችኛው እርከን ጀምሮ የነበረውን መዋቅራዊ -እኩልነት ለመስበር በቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርት ላይ ሰፊ ሥራ መሠራቱን ፕሮፌሰር ብርሃኑ አብራርተዋል፡፡

በዚህም 34 ሺህ በላይ አዳዲስ የቅድመ-አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው 4 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ነፃ የትምህርት ዕድል ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ መሠረታዊ ግብዓት የሌላቸውን ነባር ትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሻሻል በተደረገው ንቅናቄ ኅብረተሰቡ 145 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ ታሪካዊ ተሳትፎ ማድረጉን እና ለቀጣይ ትምህርት ቤቶችም አዲስ የዲዛይን ስታንዳርድ መውጣቱን አስታውቀዋል።

የብቃት ምዘና እና የፈተና ሥርዓቱን በማስተካከል በኩል የተወሰደው ወሳኝ እርምጃ ኩረጃን እና ሥርቆትን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ማስቻሉን የገለጹት ፕሮፌሰሩ፣ በልፋት እና በችሎታ ብቻ ውጤት የሚገኝበት መተማመን መፈጠሩን አስረድተዋል።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዘርፍም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ራስ-ገዝ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን አስታውሰው፣ ሌሎች ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች በቀጣይ ዓመት ወደ ራስ-ገዝነት እንደሚሸጋገሩ አብስረዋል።

ተቋማቱ ከዘር እና ከመንደር አስተሳሰብ ወጥተው ብቃትን ብቻ ማዕከል ያደረገ አሠራር እየተገነባላቸው መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።

አዲሶቹ ተመራቂዎች ያገኙት የምረቃ ዲፕሎማ የተቆለፈ በር መክፈቻ እንጂ የጉዟቸው ማጠናቀቂያ አለመሆኑን መገንዘብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በሄዱበት ስፍራ ሁሉ ችግር ፈቺ፣ ማኅበረሰቡን የሚያንጹ እንዲሁም የእውነት፣ የፍትሕና የቅንነት አምባሳደሮች እንዲሆኑ ቻንስለሩ አደራ ብለዋል።

በለሚ ታደሰ