በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በአዲስ አበባ የተያዙ ግቦችን ሙሉ ለሙሉ ማሳካት መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ኀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀምበር (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በሌሎች ዘርፎች እንደተመዘገበው ውጤት ሁሉ፣ በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥም በተሠሩ ሥራዎች በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል፡፡
በመንግሥት አገልግሎት ውስጥ ዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ አሰራርን በመገንባት፣ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ሰፊ ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በሚገኙ 1 ሺህ 222 ዋና እና ንዑስ አገልግሎቶች መካከል፣ 354 የሚሆኑትን ዲጂታል የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ዘመናዊ ማድረግ መቻሉን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
በዲጂታል የአሠራር ሥርዓት በመግባታቸው ከፍተኛ ጠቀሜታ እየሰጡ የሚገኙ የውክልና፣ ንግድ ፈቃድ አገልግሎቶች፣ የዲጂታል የጤና ክፍያ ስርዓት፣ የፍጆታ ክፍያዎች እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎቶች መኖራቸውም ተጠቁሟል።
በከተማ አስተዳደሩ የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽነትን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ በየጊዜው በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያጋጥሙ የነበሩ የኔትዎርክ መቆራረጦችን በመቀነስ የተገልጋይ እርካታን መጨመር እንደተቻለም ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ በተበታተነ መልኩ ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን በተቀናጀ መልኩ በጥራትና በፍትሐዊነት ለመስጠት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 በተቋማት እና በሕዝቡ መካከል መተማመንን በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ያሉት ኀላፊው፤ የተቀመጡ ግቦች በማሳካት አገልግሎቶችን ይበልጥ ፈጣን እና ፍትሐዊ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በመሀመድ ፊጣሞ