Search

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የሀገራችንን ገጽታ በሚያጎሉ ታላላቅ ሁነቶች ይከበራል

ሓሙስ ታኅሣሥ 16, 2018 420

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተመሰረተበትን 90ኛ ዓመት፥ “የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ የነፃነትና የአንድነት ምልክት” በሚል መሪ ቃል ከጥር 15 - 19/2018 ዓ.ም ዓለም አቀፍ ይዘት ባላቸው ታላላቅ ሁነቶች እንደሚከበር ተገልጿል።

ክብረ በዓሉ የሚያካትታቸውን ሁነቶች አስመልክቶ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የ1ኛ አየር ምድብ አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ብሩክ ሰይፉ እና የአየር ኃይል ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል መሰረት ጌታቸው ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በክብረ በዓሉ፥ “የአንበሶች ሰማይ፣ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል የተባበሩት አረብ ኢሚሬት፣ የሩስያ፣ የሞሮኮ እና የቼክ ሪፐብሊክ አየር ኃይሎች በጋራ ሁለተኛውን የጥቁር አንበሳ የአየር ትርዒት 2026 እንደሚያቀርቡ ተገልጿል።

በተጨማሪም፥ የኢትዮጵያ አየር ኃይል እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የአሜሪካ፣ የቻይና፣ የህንድ እና የደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎች እንዲሁም በአቪዬሽን ዘርፍ የተሰማሩ ከ25 በላይ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ኤክስፖ “የወደፊቱን የአቪዬሽን አቅም በጋራ እንገንባ” በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድ ተጠቅሷል።

ከዚህ ባሻገር፥ ከ38 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የአየር ኃይል አዛዦች እና የዘርፉ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት፥ "የጋራ ሥራዎቻችንን አጠናክረን የተረጋጋ ዓለም እንገንባ" በሚል መሪ ኃሳብ ለ3ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ አየር ኃይል አዘጋጅነት የአፍሪካ አየር ኃይሎች ፎረም እንደሚካሄድም በመግለጫው ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ያለፈውን በመዘከር፣ አሁናዊ የተቋሙን ቁመና በማቅረብ፣ የደረሰበትን ሁሉን አቀፍ ዝግጁነት በማሳየት የሀገራችንን ገጽታ ለማጉላት እና የኢትዮጵያን የአቪዬሽን ተስፋ ለማለምለም በሚያስችሉ ዝግጅቶች እና ተግባራት እንደሚከበር የመላክቷል።

ህብረተሰቡ በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ያገለገሉ እና እያገለገሉ ያሉ ጀግኖችን እንዲያከብርና እንዲዘክር እንዲሁም በዚህ አስደናቂ እና ታሪካዊ በዓል ላይ እንዲታደም የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጥሪውን አቅርቧል።

ህብረተሰቡ በበዓሉ ላይ ለመታደም እንዲሁም የዝግጅቱን ዝርዝር ለማየት https:/www.etaf90years.com ድረ-ገፅ በመግባት ትኬቶችን መግዛት እንደሚችልም የኢፌዴሪ አየር ኃይል አስታውቋል።

በሳምሶን በላይ

#EBC #ebcdotstream #EthiopianAirlines #90years #anniversary