Search

የትህነግ ቡድን ሕዝብን በርሃብ በመቅጣት ለፖለቲካ መሣሪያነት የመጠቀም ተግባሩን ዳግም በትግራይ ሕዝብ ላይ እያሳየ ነው

ሓሙስ ታኅሣሥ 16, 2018 428

የትህነግ ቡድን ሕዝብን በርሃብ በመቅጣት ለፖለቲካ መሣሪያነት የመጠቀም ተግባሩን ዳግም በትግራይ ሕዝብ ላይ እያሳየ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ተናገሩ።
የትህነግ ቡድን የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል በመጠለያ ማዕከላትና በልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር የሚያቀርበውን ሰብዓዊ ድጋፍ ለተፈለገው ዓላማ እንዳይወል እያደረገ እንደሚገኝም የሰሞኑ የህፃፅ መጠለያ ጣቢያ ማስረጃ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የትህነግ ሕገወጥ ቡድን የትግራይን ሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶችና ሰብዓዊ ቀውሶች ለፖለቲካ ዓላማ የመጠቀም ልማድ አዲስ ክስተት ሳይሆን የቀደመ ታሪኩና መገለጫው ነው።
ትህነግ ቡድን የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ለመሳብ በትግራይ ክልል በመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ወገኖች የሚቀርብን ሰብዓዊ ድጋፍ በመንጠቅ ድራማዊ ፕሮፓጋንዳ እያስተጋባ መሆኑንም አስረድተዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የፌደራል መንግስት በግልጽ መረጃና ማስረጃ የሚልከው ሰብዓዊ ድጋፍ የት እንደገባ መጠየቅ እንዳለበት እና በቡድኑ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ መደናገር እንደሌለበትም አንስተዋል።
የትህነግ ሰብዓዊ ድጋፍ ለፖለቲካ ዓላማ ለማዋል የሚያደርገውን ጥረት ሁሉም ሊገነዘበው እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
የፌደራል መንግስትም በትግራይ ክልል አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በዚህም በትግራይ ክልል ከባለፈው ጥር 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታኅሳስ ወር 2018 ዓ.ም ድረስ ሁለት ሚሊየን ኩንታል በገንዘብ ሲተምን 32 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሰብዓዊ ድጋፍ መሰራጨቱን አስታውቀዋል።
ይህም የፌደራል መንግስት ዜጎች ሰብዓዊ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ያለውን ጠንካራ አቋም በተግባር የሚያረጋግጥ መሆኑንም ነው ያብራሩት።
የትህነግ ቡድን በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፉ ተደራሽ እንዳይሆን በማስተጓጎል፤ ድጋፉን ከችግረኛ ዜጎች በመንጠቅ ዳግም የሕዝብ ጠላትነቱን እያረጋገጠ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ቡድኑ ይህ አልበቃ ብሎት ለእያንዳንዱ ድጋፍ ፈላጊ ዜጋ ከሚሰጥ የፍጆታ ድርሻ ላይ መዋጮ እንደሚሰበስብም ነው የተናገሩት።
የትህነግ ቡድን በሰብዓዊ ድጋፍ ስም በዜጎች ላይ የሚፈጽመው አስነዋሪ ድርጊት ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ያለውን የተላላኪነት ጥግ በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ የድጋፍ ጥሪ ባላቀረበበት ሁኔታ በማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች በቡድንም ሆነ በተናጠል የሚደረጉ የድጋፍ ማሰባሰብ ዘመቻ የአሰራር ስርዓትን የጣሱ ህገ-ወጥ አካሄዶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህም የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም ሰብዓዊ ድጋፍ በማሰባሰብ ላልተገባ ዓላማ እያዋሉ የሚገኙ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባም አሳስበዋል።