Search

ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሥራም ተፅዕኖም የፈጠሩ ጀግኖች

ዓርብ ታኅሣሥ 17, 2018 1607

በኢትዮጵያ ውስጥ የዲጂታል ቴክኖሎጂ (Digital Technology) መስፋፋትን ተከትሎ ትንሽ የማይባሉ ወጣቶች የዕለት ተዕለት ሕይወት፣ የሥራ ዕድል እና የፈጠራ ችሎታ በከፍተኛ ሁኔታ እየተቀየረ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየታየ የመጣው የኢንተርኔት ተደራሽነት እና የስማርት ስልኮች መስፋፋት ለወጣቶች አዳዲስ በሮችን ከፍቷል።

ወጣቶች እውቀት እና ክህሎታቸውን ተጠቅመው በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም በቴክኖሎጂ ሥራን ከመፍጠር ባሻገር ተፅዕኖ መፍጠር እየቻሉ ነው፡፡

ከዚህ በፊት የነበረው "ተመርቆ የመንግሥትን ሥራ መጠበቅ" አስተሳሰብ እየተቀየረም ነው። ወጣቶች ቴክኖሎጂን በመጠቀም የራሳቸውን ሥራ እየፈጠሩ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ መፍጠር እየቻሉ መሆናቸውን ለተመለከተ አንድ አረጋጋጭ ነው፡፡

በዚህ ዘርፍ ታዲያ ብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ሥራ እየሰሩ አንዳንዶቹም ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። ጆኤል ጣልአርጌ በቴክኖሎጂ ተፅዕኖ መፍጠር ከቻሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መካከል አንዱ ነው፡፡

ጆኤል በኢትዮጵያ ውስጥ ወጣቶች ቴክኖሎጂን እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው በማስተማር እና ግንዛቤ በመፍጠር በኩል ትልቅ ተፅእኖ እያሳደረ ያለ ወጣት ሥራ ፈጣሪ ነው።

ወጣቱ በአሁን ወቅት ዲጂታል ኮንስትራክት የተሰኘ የሶፍት ዌር፣ የዌብሳት እንዲሁም የዲጂታል ማርኬቲንግ ሥራን በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ካሉ ድርጅቶች ጋር የሚያከናውን ድርጅት ባለቤት ነው፡፡

ዛሬ ላይ ለደረሰበት ስኬት መነሻው ለመጀመሪያ ጊዜ በዳታ በማይሰራ ሁዋዌ ስልክ መኝታ ቤቱ ቁጭ ብሎ የሚዲያ ይዘት መፍጠር መጀምሩ መሆኑ ጆኤል ያስታውሳል፡፡

ከብዙ ከፍታና ዝቅታ ጉዞ በኋላ ታዲያ በአሁን ወቅት በሶሻል ሚዲያ በሚሰራቸው ይዘቶች እና ቁም ነገር አዘል ፕሮግራሞች ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኗል። በዚህም ታዋቂው ቢሊየነር ጃክ የአፍሪካ ሥራ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት ባቋቋመው እና በጠቅላላው 1.5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት በሚያበረክተው Africa’s Business Heroes (ABH) መድረክ ላይ ኢትዮጵያዊው የቴክኖሎጂ ይዘት ፈጣሪ ጆኤል ጣልአርጌ (Joel Talargie) ሀገራችንን ወክሎ ተጋብዟል ፡፡

ጆኤልበዚህ መድረክ ስገኝ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፤ ከዚህ ቀደም 2023 ለመጀመሪያ ጊዜ በምሰራቸው የዲጂታል ቴክኖሎጂ አዘል ኮንተንቶች አማካኝነት አግኝተውኝ ግብዣውን አቅርበውልኝ በዚሁ መድረክ ላይ ተገኝቼ ነበርሲል ከኢቢሲ ዶት ስትሪም ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል፡፡ ይህም ወጣቱን በዚህ ታላቅ አህጉራዊ መድረክ ላይ በዚህ ደረጃ የተሳተፈ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ሦስት መስፈርቶችን ማሟላትን በሚጠይቀው የአፍሪካ ቢዝነስ ሂሮ የሥራ ፈጣሪዎች ውድድር ላይ አፍሪካዊ መሆን፣ የንግድ ድርጅቱ በአፍሪካ ውስጥ በህጋዊ መንገድ የተመዘገበ እና በአፍሪካ ውስጥ የሚገኝ መሆን የሚጠበቅበት ሲሆን የሚወዳደረው ድርጅት ለሶስት አመታት በሥራ ላይ የቆየ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ አሸናፊ ለመሆን ለማህበረሰበብ ጠቃሚ የሆነ እንዲሁም ችግር ፈቺ ፕሮጀክት መፍጠርም ይጠይቃል፡፡

በአፍሪካ ቢዝነስ ሂሮ ውድድር ላይ በስፋት ከሚሳተፉት ሀገራት መካከል ናይጄሪያ ቀዳሚ ሀገር ናት፡፡ ይህ ውድድር ሁሉንም የአፍሪካ ሀገራት የሚያካትት ቢሆንም ኬንያ፣ ግብፅ፣ እና ደቡብ አፍሪካ  ናይጄሪያን በመከተል በብዛት ለመወዳደር እንደሚያመለክቱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አሁን ግን ኢትዮጵያውያንም በዚህ ውድድር ላይ እየተሳተፉ ሲሆን በአፍሪካን ቢዝነስ ሂሮ ውድድር ላይ ከተሳተፉ ኢትዮጵያውያን ሥራ ፈጣሪዎች መካከል ጠብታ አምቡላንስ በአውሮፓውያኑ 2020 ከምርጥ 10 የፍፃሜ ተወዳዳሪዎች አንዱ በመሆን አሸናፊ ሆኗል፡፡

በአውሮፓውያኑ 2022 በተደረገው ውድድር ከምርጥ 10 አሸናፊዎች ውስጥ መካተት የቻለው ኢትዮጵያዊ የሥራ ፈጠራ ገበያ የተሰኘው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ነው። ገበያ (Gebeya) የአፍሪካን የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ከዓለም አቀፍ የሥራ እድሎች ጋር የሚያገናኝ መድረክ በመሆኑ ለኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን ወክለው በመቅረብ አሸናፊ ሆነዋል።

ይህ ድርጅት 2022 በዚህ መድረክ ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ ቀርቦ አሸናፊ የነበረ ቢሆንም በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት 2025 ውድድሩን ስፖንሰር ማድረግ የቻለም ድርጅት ለመሆን በቅቷል፡፡

እንደዚህ አይነት ውድድሮች ሲዘጋጁ አብዛኛው ሥራ ፈጣሪ ሃሳቡ ቢኖረውም ሥራውን ወደ ገበያ ለማምጣት የሚቸግራቸው መነሻ ካፒታል እንደ (ABH) ያሉ መድረኮች ለአሸናፊዎች የገንዘብ ሽልማት በመስጠት ድርጅታቸውን እንዲያሳድጉና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲገዙ ትልቅ አቅም ይፈጥሩላቸዋል።

አንድ ሥራ ፈጣሪ በእንደዚህ አይነት ትልቅ መድረክ ላይ ለፍጻሜ ሲደርስ ንግዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ ከማገዙም ባሻገር ሌሎች ባለሀብቶች (Investors) በድርጅቱ ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ይረዳል፡፡

መድረኮቹ ለሥራ ፈጣሪው ድልድይ በመሆን ከአካባቢያዊ ንግድ ወደ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንዲሸጋገሩ ዕድል ይፈጥራል። ጆኤልም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ በመሆን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥም የማህበረሰብን ችግሮች የሚፈቱ እንዲሁም በቀላሉ አግልግሎት ማግኘት የሚያስችሉ አማራጭችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካኝነት ማግኘት እየተቻለ ነው፡፡

ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ጋር በመናበብ እንደ ራይድ (Ride) እና ፈረስ (Feres) ያሉ የትራንስፖርት መተግበሪያዎች በሺህዎች የሚቆጠሩ አሽከርካሪዎችና ባለሙያዎች የሥራ ዕድልን ፈጥረዋል።

ቴክኖሎጂን በመጠቀም እንደ በዩ (BeU) እና አሻም (Asham) ያሉ ድርጅቶች የምግብና የሸቀጥ አቅርቦትን በማሳለጥ ለወጣቶች የሞተር ብስክሌት ስምሪትና የመላኪያ ሥራዎችን አመቻችተዋል።

በተጨማሪም ብዙ ወጣቶች በቴሌግራም (Telegram) ፌስቡክ (Facebook) እና ቲክቶክ (TikTok) ላይ ምርቶቻቸውን (ልብስ፣ ጌጣጌጥ፣ አገልግሎት) በመሸጥ ራሳቸውን የሚችሉ ወጣቶች ብዙዎች ናቸው።

ከሀገር ውስጥ አልፈው በዓለም አቀፍ ገበያ የአገር ውስጥ የእጅ ጥበብ ውጤቶችና ሌሎችንም በዓለም አቀፍ የገበያ ድረ-ገጾች እንደ (Etsy) ያሉ የገበያ ድረ ገጾች ላይ እንዲሸጡ ዕድል ከፍቷል።

ወጣቶች በዩቲዩብ (YouTube) እና በተለያዩ መድረኮች የኮዲንግ፣ የግራፊክ ዲዛይን፣ እና የዲጂታል ማርኬቲንግ ክህሎቶችን በቤታቸው ሆነው እንዲማሩና በዓለም አቀፍ ደረጃ "Freelance" (በራሳቸው ተቀጥረው) እንዲሰሩ አስችሏቸዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋት የሥራ ፈጠራን ከማገዝ እና ከማበረታታት ባሻገር ዘመናዊ እና ፈጣን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖር ጉልህ አበርክቶ አድርጓል፡፡

ወጣቶች የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩ ብቻ ሳይሆን  ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንድትሆን ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

በንፍታሌም እንግዳወርቅ