Search

ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበትን መንገድ የሚቀይሰው ሀገራዊ ምክክር

ማክሰኞ ታኅሣሥ 21, 2018 370

ቁርሾን እና አለመግባባትን ከዜጎች መካከል ለማስወገድ በማለም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ ከሦስት ዓመታት በላይ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቶ ዋናውን ምክክር ለማካሄድ ተቃርቧል።
ለሀገራዊ ዕድገት እንቅፋት የሆኑ በርካታ ችግሮች ዋጋ አስከፍለዋል፤ በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ሀገራዊ ምክክር የግድ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ሥራ ተጀምሯል።
ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ያለመው ሀገራዊ ምክክሩ፤ ዋና ዓላማው በየቦታው የሚታዩ አለመግባባቶችን እና ግጭቶችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በምክክር በመዝጋት ሁሉም አሸናፊ ሆኖ የሚወጣበትን መንገድ መቀየስ ነው።
እስካሁን ባለው የሀገራዊ ምክክር ሂደት የአጀንዳ ልየታና የተወካዮች ምርጫ በአብዛኞቹ ክልሎች ተከናውኗል።
በሁሉም ክልሎች ከሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከልዩ ልዩ ማኅበራት፣ ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ እና ከተለያዩ አካላት ጋር የእርስ በእርስ ምክክሮች የተደረጉ ሲሆን፤ በትግራይ ክልልም በቀጣይ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በዋና ዋና ሀገራዊ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ምክክር በማካሄድ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያለመው ዋናው ምክክር በመጪው ጥር መጨረሻ ይጀመራል።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ አበሻ ሽርኮ (ዶ/ር) ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ባለፉት ዓመታት በሀገራዊ ምክክሩ በርካታ ልምዶች እና ተሞክሮዎች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።
የሐሳብ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ ተወያይቶ የመፍታት ልምድ ብዙም እንዳልነበር በመግለጽ፤ በሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ይህን መቅረፍ ተችሏል ብለዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ጥሩ ተስፋን ይዞ መምጣቱን ያመላከቱት መምህሩ፤ እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ እና ሩዋንዳ ያሉ ሀገራት ባካሄዱት ሀገራዊ ምክክር ቁርሾዎችን እና አለመግባባቶችን በመፍታት ዛሬ ላሉበት ደረጃ መድረሳቸውን ለአብነት አንስተዋል። ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለኢትዮጵያ ሰላማዊ የሀገር ግንባታ እና ለውጥ መትጋት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑ እሙን ነው።
 
በሜሮን ንብረት