"እኛ በነበርንበት ጊዜ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ንግሥት ነበረች ሊባል ይችላል። የባሕር ኃይላችን በጣም ጠንካራ እና የሚፈራ ነበር። ዛሬ የባሕር በር የለንም ስንባል እንደ መርከበኛ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያዊም ትልቅ ስብራት ነው የሚሰማን።ባሕር ለኢትዮጵያ የቅንጦት አይደለም፤ የኅልውና ጉዳይ ነው። ያለ ባሕር በር ዕድገት እና ብልጽግናን ማሰብ በጣም ከባድ ነው"። - (የቀድሞው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አባላት)
በ1975 ዓ.ም በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ለባሕር ኃይል ምልመላ ተጀመረ። የባሕር ኃይሉን ለመቀላቀል ከተመዘገቡት በመቶ የሚቆጠሩ ወጣቶች መካከልም ጥብቅ የሆነውን የጽሑፍ እና የሕክምና የብቃት መስፈርት አልፈው ከተመረጡት ጥቂት ወጣቶች መካከል ከደብረ ማርቆስ የመጣው መሪ መርከበኛ (Leading Seaman) ዘላለም ምንያምር እና ከአዲስ አበባ የተመረጠው ሊዲንግ ሲማን እስክንድር ገብረዮሐንስ ይገኙበታል።
እነዚህ ወጣቶች ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ፈተናውን አልፈው ብቁ ከሆኑ ምልምል አባላት ጋር በመሆን አስመራ ወደሚገኘው የባሕር ኃይል ማሰልጠኛ ጣቢያ አመሩ።
ሁለቱ መርከበኞች በምፅዋ ማሰልጠኛ ለስምንት ወራት የአካል ብቃት እና ወታደራዊ ሳይንስን ያካተተ ሥልጠና ተከታትለዋል።
በኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ውስጥ ልዩ ቦታ በነበረው የማሪን ኮማንዶ ሥልጠና ብቁ ለመሆን ደግሞ፣ ሠልጣኞቹ በባሕር፣ በየብስ እና በአየር ላይ ተዋጊ እንዲሆኑ በልዩ ሁኔታ ይሠለጥኑ ነበር።
የዚህ የማሪን ኮማንዶ ዋና ተግባር 'Amphibious Operation' ወይም የየብስ እና የባሕር ጥምር ውጊያዎችን ማካሄድ ነው። ይህም መርከበኛ ሆኖ ነገር ግን እንደ እግረኛ ጦር ምድር ላይ ወርዶ የመዋጋት ብቃት እንዲኖር የሚያደርግ ፈታኝ ልምምድ ነው።
ሥልጠናው በጣም ከባድ እንደነበር የሚያስታውሱት የያኔዎቹ ወጣቶች፣ ባሕር ውስጥ ረጅም ርቀት መዋኘት፣ ከመርከብ ላይ በገመድ መውረድ፣ በትንንሽ ጀልባዎች ድንገተኛ ጥቃት ማድረስን እንደሚያካትት ይገልጻሉ።
“እኛ በምፅዋ አካባቢ ነበር ሥልጠናውን የወሰድነው። በወቅቱ የነበሩት አሠልጣኞችም በጣም ብቁ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ማሪን ኮማንዶ ማለት በማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የተሰጠውን ተልዕኮ የሚወጣ ኃይል ማለት ነው።” በማለት ይህን መሳይ ብቃት ያለው የባሕር ኃይል ለማፍራት በጣም ከባድ ሥልጠና ይወስዱ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በተጨማሪም "Navigation" ወይም መርከብን የመምራት ትምህርት ሌላው ወሳኝ ከፍል ነበር። ኮምፓስን እንዴት መጠቀም እንደሚገባ፣ ካርታ (Chart) ማንበብ እና በከዋክብት ተጠቅመው አቅጣጫን መለየት የትምህርቱ ዋና ክፍል ሲሆን በወቅቱ እንደ አሁኑ የGPS ቴክኖሎጂ ባለመኖሩ ይህ እውቀት መሠረታዊ ነበር።
መርከቦች እንዳይጋጩ የሚደነግገው የባሕር ላይ ትራፊክ ደንብ "Rules of the Road" የሚባለው መርከበኞቹ በቃላቸው የመያዝ ግዴታም ነበረባቸው።
ሁለቱ መርከበኞች ስለ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ኩራት ስለነበረችው "ጦር መርከብ ኢትዮጵያ“ ሲያስታውሱም፤ መርከቧ ግዙፍ እና አስፈሪ እንደነበረች ይናገራሉ። 310 ጫማ ርዝመት እና 2 ሺህ 800 ቶን ክብደት ያላት ይህች መርከብ፣ በሰዓት 33 ኪሎ ሜትር የመጓዝ አቅም የነበራት ሲሆን 120 መርከበኞችን መያዝ ትችል ነበር።”
የራሷ መኝታ፣ ምግብ ቤት፣ ሻወር እና የሥራ ክፍሎች ያሏት ሲሆን ከ"ሲማን ሪክሩት" አስከ "ሬር አድሚራል" የሚደርስ ወታደራዊ አርከን ያላቸውን ባለሙያዎች የያዘች "ተንሳፋፊ መንደር“ ስለመሆኑ ያስታውሳሉ።
ይህች ከአሜሪካ መንግሥት የተሰጠች መርከብ፣ ቀደም ሲል "USS Orca (AVP-49)" የሚል ስያሜ የነበራት እና በኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ውስጥ የሥልጠና እና የውጊያ ማዕከል ሆና አገልግላለች።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መቋቋምን ተከትሎም በ1950ዎቹ አጋማሽ ወደ ኢትዮጵያ መጥታ "ጦር መርከብ ኢትዮጵያ" የሚል አዲስ ስያሜ ተሰጥቷት የሀገሪቱ የባሕር ኃይል ዋነኛ የሥልጠና እና የውጊያ መርከብ ሆና አገልግላለች።
"ጦር መርከብ ኢትዮጵያ በወቅቱ በጣም የታጠቀች ነበረች። ከ5-ኢንች ጋን በተጨማሪ 40 ሚሊ ሜትር እና 20 ሚሊ ሜትር ፀረ-አውሮፕላን መሣሪያዎች ነበሯት። እነዚህ መሣሪያዎች መርከቧን ከአየር ላይ ጥቃት የሚከላከሉ ናቸው።”
በተጨማሪም የባሕር ውስጥ ጥቃትን ለመከላከል የሚያገለግሉ "Depth Charges" ነበሩ። እነዚህ የባሕር ውስጥ ሰርጓጅ መርከቦችን ለማጥቃት የሚያገለግሉ ቦምቦች ናቸው። መርከቧ በማንኛውም መልኩ ራሷን መከላከል የምትችል እና ጥቃት መሰንዘር የምትችል ግዙፍ የጦር ምሽግም ነበረች። ጠላትን ከሩቅ ለመለየት እና የባሕር ውስጥ ሁኔታን ለማወቅ የሚረዳ ሶናር ራዳር ተገጥሞላታል።
መርከቧ ውስጥ ያለው "Engine Room" ወይም የሞተር ክፍል በጣም ግዙፍ ነው። እዛ ውስጥ የሚሠሩ መርከበኞች ከፍተኛ ሙቀት እና የሞተሩን ድምፅ ተቋቁመው ይሠሩ ነበር። በአጠቃላይ ሁሉም የመርከቡ አባላት በተመደቡበት የሥራ ዘርፍ ሥራቸውን በከፍተኛ ትጋት እና የሀገር ፍቅር ስሜት ይከውኑ ነበር” በማለት የኢትዮጵያ ኩራት ስለነበረችው “ጦር መርከብ ኢትዮጵያ” ተናግረዋል።
የባሕር ኃይል አባላቱ በወቅቱ በባሕር ኃይሉ ይተገበር ስለነበረው ጥብቅ የሆነ ዲሲፕሊን ሲገልጹ፦
"በጣም ጥብቅ የሥነ- ምግባር ደንብ ነበር። በሥልጣን ተዋረድ የሚበልጥህ ማንኛውም አባል ሲያልፍ ሰላምታ መስጠት እና ታዛዥ መሆን ግዴታ ነበር። መርከብ ላይ ጠዋት ሁለት ሰዓት ላይ የሰንደቅ ዓላማ መስቀል ሥነ-ሥርዓት ወይም 'Colors' ይከናወናል። በዚያ ሰዓት መርከቧ ላይ ያለ ማንኛውም ሰው ባለበት ቆሞ ለሰንደቅ ዓላማው ሰላምታ መስጠት አለበት፤ ምከንያቱም ያ ምልክት የሀገር ክብር ነውና።
መርከቧ ለ24 ሰዓት አትተኛም፤ ሞተሯ አይጠፋም፣ ጥበቃው አይላላም። በአራት ሰዓት ልዩነት በፈረቃ (Watch) እየተቀያየርን በመሥራታችን በመካከላችን ትልቅ መተማመን ነበረ" ይላሉ።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በነበሩበት ስላሳለፉት ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብለው ትውስታቸውን የሚናገሩት የቀድሞ ባሕር ኃይል አባላት በመርከብ ላይ ያለው ሕይወት ከየብስ ሕይወት በጣም የተለየ እንደሆነ ነው የሚናገሩት።
መርከብ ላይ ስትሆን መጀመሪያ ጠባብ ቦታ ናት። በዛች ጠባብ ቦታ ላይ ነው ሁሉንም ነገር የምታከናውነው። መኝታህ እዛው ነው፣ ምግብህ እዛው ነው፣ ሥራህ እዛው ነው። እና በጣም የሚገርመው ነገር መርከብ ላይ ስትሆን እንደ አንድ ቤተሰብ ነው የምትኖረው።
በመርከብ ላይ በምታሳልፈው እያንዳንዱ ጊዜ ያንተ ሕይወት በጓደኛህ እጅ ላይ ነው ያለው። አንዱ ለአንዱ ጥንቃቄ ያደርጋል። መርከብ ላይ ስትሆን ሀገርህን የምታየው በዛች በምትመራት መርከብ ውስጥ ነው። መርከቧ የሀገርህ ሰንደቅ ዓላማ ናት። የትም ቦታ ስትሄድ ያቺ መርከብ ኢትዮጵያን ነው የምትወክለው። እና ያ ስሜት በጣም የተለየ ስሜት ነው።
መርከብ ላይ ስትሆን ቤተሰብ ይናፍቀሃል። ነገር ግን ባሕር ላይ ረጅም ጊዜ ስትቆይ ደግሞ መርከቧ ራሷ ቤተሰብህ ትሆናለች። ከባሕር ወጥተህ የብስ ላይ ለረጅም ጊዜ ስትቆይ ደግሞ ባሕሩ ይናፍቀሃል።
ያ ማዕበሉ፣ ያ የውኃው ድምፅ፣ ያ የጓደኝነት መንፈስ በጣም ይናፍቃል። መርከብ ላይ ሕይወት በጣም ሥልታዊ ነው። ለምሳሌ "Piping" የሚባል አለ፤ በመለከት ወይም በፉጨት የሚሰጥ ትዕዛዝ ማለት ነው። ለምግብ፣ ለሥራ፣ ለሰላምታ ሁሉ የራሱ የሆነ ድምፅ አለው። በዛ ድምፅ ነው መርከቧ የምትመራው።
"መርከብ ላይ ምግብ በጣም በሥርዓት ነው የሚዘጋጀው። "Galley" የሚባል የምግብ ማብሰያ ክፍል አለ። እዛ ውስጥ ያሉ መርከበኞች ለዛ ሁሉ ሰራተኛ ቁርስ፣ ምሳ እና እራት ያዘጋጃሉ። የሚገርመው ነገር መርከብ ላይ ምግብ አይጎድልም። ምክንያቱም መርከበኛው በቂ ጉልበት እና ጥንካሬ እንዲኖረው ይፈለጋል።
መርከብ ላይ በጣም የሚከለከለው ነገር አልኮል ነው። አንድ መርከበኛ ሥራ ላይ እያለ አልኮል መጠጣት በፍጹም አይፈቀድለትም። ምክንያቱም በባሕር ላይ የሚፈጠር ድንገተኛ አደጋ ካለ ንቁ መሆን አለብህ። መርከቧን እና ጓደኞችህን መጠበቅ አለብህ።
በዚህ ሁኔታ ነበር የምንንቀሳቀሰው። ወደ ሌላ ሀገር ስንጓዝ ደግሞ ልክ ወደቡ ላይ እንደደረስን መጀመሪያ የምናደርገው የሰላምታ ተኩስ መተኮስ ነው። "Gun Salute" ይባላል።
የተኩስ ሰላምታ ለዚያ ሀገር ያለህ አክብሮት መግለጫ ነው። ከዚያም የሀገርህን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገህ ትሰቅላለህ። በዚያን ጊዜ "እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ ይቺም የሀገሬ መርከብ ነች" ብለህ በኩራት ነው የምትቆመው። ሰዎች ወደ መርከቧ መጥተው ሲጎበኙ እና የኢትዮጵያን ጥንካሬ ሲያዩ ትልቅ ደስታ ይሰማሃል" ይላሉ ሊዲንግ ሲማን ዘላለም ምንያምር እና ሊዲንግ ሲማን እስክንድር ገብረዮሐንስ
እነዚህ የግዙፉ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አባላት ሆነው ያሳለፉት መርከበኞች ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር አድርገውት በነበረው ቆይታ ማጠቃለያ ላይ ሐሳባቸውን ሲገልጹ፦
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን መልሳ ማቋቋሟ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አፅንኦት የሰጡ ሲሆን ምክንያቱን ሲያስቀምጡም የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የንግድ እንቅስቃሴያችን በባሕር ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል።
በቀጠናው ላይ ያለውን ጂኦ-ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ስንመለከት፣ ያለ ባሕር ኃይል የሀገርን ደኅንነት እና ጥቅም ማስጠበቅ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው።
እኛ በነበርንበት ጊዜ የባሕር ኃይሉ የነበረው ቁመና ለሀገሪቱ ትልቅ ክብር ነበር። ዛሬ ደግሞ ካለንበት የሕዝብ ብዛት እና ካለን ሰፊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አንፃር የባሕር ኃይል መኖሩ ለብሔራዊ ጥቅማችን ወሳኝ ነው።
ስለዚህ አሁን መንግሥት የጀመረው ጥረት በጣም የሚበረታታ ነው። እኛም እንደ ባለሙያ ያለንን ልምድ እና እውቀት ለማካፈል ሁሌም ዝግጁ ነን" ብለዋል።
ወጣቱ ትውልድ ስለ ባሕር ኃይል ታሪካችን እና ስለ ባሕር በር አስፈላጊነት በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል። ባሕር ለኢትዮጵያ ትንሣኤ ነው። ይህንን ደግሞ ሁላችንም በጋራ ልንሠራበት ይገባል።
እኛ በነበርንበት ጊዜ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ንግሥት ነበረች ሊባል ይችላል። የባሕር ኃይላችን በጣም ጠንካራና የሚፈራ ነበር። ዛሬ የባሕር በር የለንም ስንባል እንደ መርከበኛ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያዊም ትልቅ ስብራት ነው የሚሰማን። ባሕር ለኢትዮጵያ የቅንጦት አይደለም፣ የኅልውና ጉዳይ ነው። ያለ ባሕር በር ዕድገት እና ብልጽግናን ማሰብ በጣም ከባድ ነው" በማለት ነው ሐሳባቸውን ያጠቃለሉት።