Search

ውጤት የታየበት የግብርና ሽግግር

ረቡዕ ታኅሣሥ 22, 2018 286

የመደመር መንግሥት ወሳኝ ሥራዎችን ካከናወነባቸው መስኮች መካከል የግብርና ሽግግር በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግብርና የኢኮኖሚያችን መሠረት ብቻ ሳይሆን የሀገራዊ ክብራችንና የነጻነታችን መገለጫ ነው በማለት በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ለዘመናት የነበረባትን የተረጂነት ታሪክ በመቀየር፣ በምግብ ራሷን እንድትችልና ለዓለም ገበያ ጭምር ምርት እንድታቀርብ የተቀረጹት ሌማት ትሩፋት እና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ውጤት የተመዘገበባቸው የግብርና ሥራዎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርና ለማዘመን በርካታ ሥራዎች እንደተሠሩና በመሠራት ላይም እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ድሪባ ገለቲ (ዶ/ር) ከኢቲቪ ዜና 57 አጀንዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
በዘርፉ የሰለጠኑ እና የበቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉ ግብርናው እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
በመደመር መንግሥት ትኩረት የተሰጠው ሌላኛው ጉዳይ ግብርናውን ከቴክኖሎጂ ጋር በማጣመር ማዘመን ሲሆን፤ ይህም ሽግግሩን ይበልጥ ውጤታማ አድርጎታል ይላሉ።
አዳዲስ ፖሊሲዎችን መቅረጽ እና ግብርናውን በፋይናንስ መደገፍ ከተረጂነት ወደ አምራችነት የሚደረገውን የግብርና ሽግግር ለማፋጠን የሚያግዙ ወሳኝ እርምጃዎች መሆናቸውንም አስረድተዋል።
በተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገብ መጀመራቸውን የገለጹት ዶክተር ድሪባ፤ ግብርናችን ዝናብን ብቻ ከመጠበቅ ተላቆ በዓመት ውስጥ እስከ ሦስት ጊዜ ምርት የሚመረትበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል።
አርሶ አደሩ ከበሬ እርሻ ተላቆ ወደ ሜካናይዜሽን እንዲሸጋገር የመለዋወጫ እና የጥገና ማዕከላትን ለማስፋት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም አርሶ አደሮች የሚያመርቱትን ምርት ከራስ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ እንዲያቀርቡና በኢኮኖሚው ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።
 
በሃብተሚካኤል ክፍሉ
All reactions:
56