Search

ለኢትዮጵያዊ ችግሮች ኢትዮጵያዊ መፍትሄ የሚፈለግበት ታላቁ መድረክ

ሓሙስ ታኅሣሥ 23, 2018 413

ቱርኮች "ብታጣ ብታጣ ምርኩዝህን አማክር"ይላሉ፤ ከሰው ጋር መመካከር እና ለችግሮች መፍትሄ መፈለግን ሲያመላክቱ።
"ዝምታ ጥላ ነው፤ መነጋገር ግን ብርሃን ነው" እንደሚሉት ፈረንሳዮቹም፤ ኢትዮጵያም የቁርሾዎች ማከሚያ እና የነገው ተስፋ ፋኖስ የሆነውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋና ጉባዔን ልታካሂድ ተሰናድታለች።
ኢትዮጵያ በተለያዩ ሁነቶች የታጀበ የታሪክ ማዕበል ውስጥ አልፋ፣ አዲስ የታሪክ ምዕራፍን ለመቀበል ጉድ ጉድ እያለች ነው።
በቀጣዩ ወር የሚካሄደው ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ፣ የቆዩ ቁርሾዎችን የሚያክም፣ ለትውልድ የሚተርፍ መግባባትን የሚዘራ እና የኢትዮጵያን የነገ ጉዞ የሚያቀና ወሳኝ ምዕራፍ ሆኖ ከደጃፋችን ደርሷል።
ተጠባቂው መድረክ ለዓመታት የተለፋበት፣ የብዙዎች ዕንባና ጸሎት የታከለበት የበጎ ሥራ ጥንስስም ነው።
የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግሮች ለመፍታት በጠረጴዛ ዙሪያ ከመመካከር የተሻለ አማራጭ የለም። ከመነጋገር ርቀን የምንሄድ ከሆነ ከፍታን ሳይሆን ውድቀትን ፣ ውጤት ሳይሆን ኪሳራን እንደመረጥን ይቆጠራል ይላሉ የተለያዩ ምሁራን።
"ሺህ ቢታጠቁ መታረቅ አይከፋም" ነውና ነገሩ፤ የቱንም ያህል ኃይልና ጉልበት አለን ተብሎ ቢታሰብም፣ ችግርን በሰላምና በእርቅ መፍታት ሁልጊዜም የተመረጠ መንገድ መሆኑ አያጠያይቅም።
ልዩነቶቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት አድልዎ የሌለበትና ግልጽ ውይይት ማድረግ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በተለያዩ ጊዜያት እንደገለጹት፤ ይህ ሂደት ኢትዮጵያዊ መፍትሄ ለኢትዮጵያዊ ችግር የሚፈለግበት ነጻ መድረክ ነው።
ዋና ኮሚሽነሩ ደጋግመው እንደሚያሳስቡት፣ የምክክሩ ስኬት የሚለካው በገለልተኝነትና ሁሉንም አካታች በማድረግ ላይ ነው።
በመሆኑም ኮሚሽኑ ሂደቱን ፍፁም ሰላማዊና በሃሳብ የበለፀገ ለማድረግ ያደረገው ጥረት፣ ለሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ግንባታ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው።
ይህ ታሪካዊ ጉባኤ ከሀገር ውስጥ እስከ ዳያስፖራው፣ ከምሁራን እስከ ተማሪው ድረስ ያሉ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በአንድ ቃል የሚያስተሳስር ይሆናል።
በጉባዔው ላይ የሚቀርቡት አጀንዳዎች የሕዝብን የልብ ትርታ ያዳመጡና ለዘመናት የቆዩ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ውጥንቅጦችን የሚፈቱ እንደሆኑ ይጠበቃል።
እያንዳንዱ ዜጋ ከወዲሁ ራሱን በማዘጋጀት፣ በንቃትና በኃላፊነት ስሜት መሳተፍም ይኖርበታል። ምክንያቱም ይህ ጉባዔ ተራ ስብሰባ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስን የቃል ኪዳን መድረክም ነው።
ምክክሩ የመድኃኒትነት ሚና ይኖረዋል የሚባለውም ለዚሁ ነው፤ ያለፈውን ቁስል የሚጠግን፣ የወደፊቱን መንገድ የሚጠርግና ለትውልዱ የምትመጥን ኅብረብሔራዊት ኢትዮጵያንን ለመገንባት የሚያስችል የጋራ ራዕይ ለመፍጠርም ያስችላል።
አሁን የምናደርገው ዝግጅት፣ በውይይቱ ላይ የምናሳየው ግልጽነት እና ታማኝነት፣ ነገ ለምንፈልገው ያማረ ውጤት ወሳኝ ድርሻም አለው።
ኢትዮጵያ የልጆቿን መከራ በምክክር፣ ቁጣዋን በሰላም፣ ልዩነቷን በመግባባት የምትለውጥበት ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ደርሳለች።
በዚህ ታላቅ ጉዞ ላይ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣና ለሀገራዊ መግባባቱ ስኬት በቁርጠኝነት ሊቆም እንደሚገባም የሀገር ሽማግሌዎች በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ለነገዋ የበለፀገችና የተረጋጋች ኅበረብሔራዊት ኢትዮጵያን የምንከፍለው ታላቅ የታሪክ ግብር ነውና ለስኬታማነቱ እኔም ድርሻ አለኝ እሷም ድርሻ አላት የሚል ዕሳቤና የኔነት ስሜት ያስፈልጋል።
በጌትነት ተስፋማርያም