Search

ቱሪዝምን አንዱ የኢኮኖሚ ዕድገቷ ምሰሶ አድርጋ እየሠራች ያለችው ኢትዮጵያ

ሓሙስ ታኅሣሥ 23, 2018 418

ቱሪዝም በጉልህ የሚጠቀሰው በኢኮኖሚ ልማት ውስጥ ባለው ሚናው ቢሆንም፤ ለማኅበራዊ ዕድገት፣ ለትምህርት እና ለሥራ ዕድል ፈጠራም እርሾ በመሆን ያገለግላል።

የዓለም የቱሪዝም ባሮ ሜትር (World Tourism Barometer) መረጃ እንደሚያሳየው፣ የዓለም ቱሪዝም በፈረንጆቹ 2025 አጋማሽ 5 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል።

በዓለም ቱሪዝም ባሮሜትር የቅርብ ጊዜ መረጃ መሰረት ዓለም አቀፍ ቱሪዝም 2025 ቀጣይነት ያለው እድገት አሳይቷል፡፡ በዚህም ከጥር እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ 1.1 ቢሊዮን በላይ ዓለም አቀፍ የቱሪስቶች እንቅስቃሴ ተመዝግቧል።

ቱሪዝምን አንዱ የኢኮኖሚ ዕድገቷ ምሰሶ አድርጋ በዘርፉ ላይ በርካታ ሥራዎችን እየሠራች ያለችው ኢትዮጵያም፣ 52 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ከአፍሪካ ሁለተኛ እንደሆነች የባሮ ሜትር መረጃ ያሳያል።

በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት ኢትዮጵያ 1.3 ሚሊዮን በላይ ጎበኚዎችን በማስተናገድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛውን ጎብኚ አግኝታለች፡፡ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ የጎብኚዎችን ቁጥር ወደ 2 ሚሊዮን በላይ ለማድረስ እየተሠራም ይገኛል።

እንደ ወንጪ፣ ጎርጎራ፣ ጨበራ ጩርጩራ፣ ሃላላ ኬላ እና ቤኑና ያሉ የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻዎች የበርካታ ቱሪስቶችን ቀልብ የያዙ ናቸው፡፡

የከተሞች በኮሪደር ልማት መሻሻል አንዱ የቱሪስቶችን ቆይታ የሚያራዝም ሲሆን አዲስ አበባ የአንበሳውን ድርሻ ወስዳለች፡፡ ጥንታዊቷ ሐረር፣ ጎንደር፣ ባሕር ዳር፣ ጂማ፣ ቢሾፍቱ እና ሌሎች ከተሞችም ጎብኚዎች እንዲቆዩባቸው በማድረግ ዘርፉ እየፈካ እንዲሄድ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

በዚህ ላይ በገበታ ለትውልድ በትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሌ እና ሌሎች ክልሎች ውስጥ እየተገነቡ ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች ቱሪዝም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምሰሶ የሆነበትን ምክንያት በትክክል የሚያስረግጡ ይሆናሉ፡፡

የአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ በሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የተሠሩ ማስፋፊዎችም የዘርፉን ከፍታ ለመጨመር ወሳኝ ሲሆኑ፣ አየር መንገዱ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዓለም አቀፍ ተጓዦችን ቆይታ በማራዘም የኢኮኖሚውም የገጽታ ግንባታውም ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።

የተለወጠችው እና ለበርካታ ዓለም አቀፍ እና የአፍሪካ ስብሰባዎች ተመራጭ እየሆነች የመጣችው አዲስ አበባ፣ እያስተናገደቻቸው ያሉት ታላላቅ ኮንፈረንሶችም ለዘርፉ እያበበ መሄድ ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክተዋል።

ባለፈው ዓመት ብቻ ከረሃብ ነፃ ዓለም ኮንፈረንስ፣ ለልማት የገንዘብ ድጋፍ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ፣ የአፍሪካ የሰላም ኮንፈረንስ፣ 6ኛው የአፍሪካ ብልጽግና ኮንፈረንስ፣ 46ኛው የካፍ መደበኛ ጉባኤ፣ የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ኮንፈረንስ፣ ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉበኤን ጨምሮ 150 በላይ ኮንፈረንሶች በአዲስ አበባ ተካሄደዋል።

በዓመቱ ከውጭ ቱሪስቶች በተጨማሪም 1.5 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እንደ አንድነት ፓርክ፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የወዳጅነት ፓርክ እና ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን በመጎብኘታቸው ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደተገኘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (/) መግለጻቸው ያታወሳል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት 13 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እነዚህን አካባቢዎች የጎበኙ ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፍ ቱሪዝም ስበት ማዕከል መሆኗን ማሳያ ነው።

መጪው የጥምቀት በዓል ቱሪዝምን ከፍ ከሚያደርጉ የኢትዮጵያ ሀብቶች መካከል አንዱ ሲሆን፤ እንደ ባቱ፣ ጎንደር፣ ኢራንቡቲ እና ሌሎች ጥምቀት በተለየ ሁኔታ የሚከበርባቸው አካባቢዎች እንደወትሮው ደምቀው የሚታዩበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

በለሚ ታደሰ