Search

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በጥር ወር ይጀምራል

ሓሙስ ታኅሣሥ 23, 2018 365

በአፍሪካ ትልቁ የሆነው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በጥር ወር እንደሚጀመር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አስታውቋል።

ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አቡሴራ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በ10 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገነባው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ 3 ሺህ 975 ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ነው።

የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ 60 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል።

ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ ሲጠናቀቅ አውሮፕላን ማረፊያው በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ ያስችላል።

የአውሮፕላን ማረፊያው ሁለት ዘመናዊ ተርሚናሎች፣ ሁለት የአውሮፕላን መንደርደሪያዎች፣ የአውሮፕላን ጥገና ማዕከል፣ የካርጎ ማስተናገጃ ማዕከል፣ የበረራ መቆጣጠሪያ፣ የመንገደኞች ማስተናገጃዎች፣ ዘመናዊ ሆቴሎች እና መዝናኛዎች እንዲሁም የንግድ ማዕከላት ይኖሩታል።

አውሮፕላን ማረፊያው ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በዓለም ዙሪያ ካሉ ጥቂት እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላን ማረፊያዎች አንዱ እንደሚሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገልጿል።

ለአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ ከሚያስፈልገው 10 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነው በአየር መንገዱ የሚሸፈን ሲሆን፤ 80 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በአፍሪካ ልማት ባንክ እና በሌሎች ባንኮች ፋይናንስ የሚደረግ ነው።

የአፍሪካ ልማት ባንክ የ500 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለመስጠት እና ቀሪውን ከአበዳሪ ተቋማት ለማፈላለግ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።

በአፍሪካ ትልቁ የሆነው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በፈጣን ባቡር እና በመኪና መንገድ እንዲገናኝ ተደርጎ የሚሠራ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በ4 ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

አውሮፕላን ማረፊያው በኢትዮጵያ በኩል ለሚያልፉ ዓለም አቀፍ መንገደኞችም ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል። በአፍሪካ ግዙፉን የአውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት የአውሮፕላን ማረፊያው ዲዛይን በመጠናቀቁ በጥር ወር መጀመሪያ ግንባታው በይፋ ይጀመራል ተብሏል።

አካባቢን የማይበክል ቴክኖሎጂ እና የፀሐይ ኃይል እንዲጠቀም፣ ዘላቂነት ያለው የቆሻሻ አወጋገድ እና የውኃ አጠቃቀም ሥርዓት እንዲኖረው ተደርጎ በዘመናዊ መልኩ የሚገነባው አውሮፕላን ማረፊያው በአካባቢ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያስከትል ተነግሮለታል።

ከአውሮፕላን ማረፊያው ወደ ቦሌ የሚገነባው ፈጣን መንገድ እና ዘመናዊ የባቡር መስመር የከተማ እና የገጠር ትሥሥርን በማጠናከር የአካባቢው ማኅበረሰብ ከከተማ ጋር ያለውን ግንኙት ለማሳደግ እንደሚያግዝ ይጠበቃል።

አየር መንገዱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ለመገንባት ከይዞታቸው ለሚነሱ አርሶ አደሮች 350 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ እጅግ ዘመናዊ ቪላ ቤቶች፣ ንግድን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ሕንፃዎች፣ የአግሮ-ፕሮሰሲንግ እና የመስኖ ማዕከላትን ገንብቶ ለመስጠት እየሠራ እንደሚገኝም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ታሪክ በከፍተኛ ወጪ የሚገነባው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ የአፍሪካውያንን ትሥሥር በማጠናከር የአፍሪካ ኅብረት "የተዋሀደች እና የተሳሰረች አፍሪካን እውን ማድረግ" በሚል የያዘው ራዕይ እንዲሳካ ትልቅ አቅም ይሆናል።

በላሉ ኢታላ

#EBC #ebcdotstream #EthiopianAirLines #BishoftuInternationalAirport