Search

የዲጂታል ኢኮኖሚውን አስተዋጽኦ ወደ 12 በመቶ ለማድረስ ያለመው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ

ሓሙስ ታኅሣሥ 23, 2018 336

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የሀገራችንን የዲጂታል ምህዳር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ያደረጉት ብሔራዊ ስትራቴጂ ነው።

ይህ ስትራቴጂ ከዚህ ቀደም ተግባራዊ ሲደረግ የቆየውን ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የሚተካ እና ሰፋፊ ግቦችን የያዘ ዕቅድ ነው።

በስትራቴጂው ይዘት ዙሪያ ከኢቲቪ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ ኤሌክትሮኒክስ መንግሥት ልማትና አስተዳዳር ዴስክ ሀላፊ አቶ ቴዎድሮስ ታዘዝ እንደገለፁት፥ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በዲጂታል አማራጮች የሀገራችንን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠን ዓላማ ሰንቋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ወደ ሥራ መግባቱን ተከትሎ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመው፤ በዋነኝነትም መሠረተ ልማት በማስፋፋት ረገድ አስቀድሞ በ2025 ስትራቴጂ የነበረውን በእጅጉ ለማላቅ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ 45 በመቶ የነበረውን የኢንተርኔት ተደራሽነት በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ትግበራ መጨረሻ ወደ 95 በመቶ ለማድረስ፣ እንዲሁም 5 ሺህ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በኦላይን ለመስጠት እንደሚሠራ ተናግረዋል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ማብቂያ ዲጂታል ኢኮኖሚው ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) የነበረው አስተዋጽኦ 4 በመቶ እንደነበር ጠቅሰው፤ በ2030 የዲጂታል ኢኮኖሚው አስተዋጽኦ ወደ 12 በመቶ እንዲያድግ በዕቅድ ተይዟል ብለዋል ።

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ኢትዮጵያን ለዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ገበያ ብቁ ለማድረግ ማለሙን ገልጸው፤ በሀገር ደረጃም አገልግሎቶችን ከፋይዳ ጋር በማስተሳሰር ህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል እንደሚሠራ ተናግረዋል።

ስትራቴጂው ኢትዮጵያን የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ እንዲሁም የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ በቴክኖሎጂ ለማቅለል የተቀረጸ ትልቅ ዓላማ ያለው ስትራቴጂ ነው ብለዋል።

በሃይማኖት ከበደ

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #DigitalEthiopia #DigitalEthiopia2030