Search

የኢትዮጵያ መከታ፣ የወደረኞቿ አስፈሪ የኢትዮጵያ አየር ኃይል

ዓርብ ታኅሣሥ 24, 2018 272

ኢትዮጵያ አብዛኛው ታሪኳ የጦርነት ነው፡፡ ራስን የመከላከል ጦርነት፡፡ የአትንኩኝ እና የፀረ ወረራ ጦርነት! የማንንም ድንበር ተጋፍታ የማታውቀዋ ኢትዮጵያ ሌሎች አልፈው ሲመጡባት ግን ጦርነቱን በድል ማጠናቀቅ ልማዷ ነው፡፡ በአክሱማውያን ዘመን የፐርሺያ ተስፋፊዎችን ከመከላከል ጀምሮ እስከ 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመኑ የዚያድ ባሬ ወረራ ድረስ ያሉ ጦርነቶችን በድል አጠናቅቃለች፡፡

እነዚህን ጦርነቶች ያደረገችው የማንንም ድንበር ተጋፍታ፣ የማንንም ሀብት ፈልጋ ሳይሆን ድንበሯን ገፍተው፤ ሉዓላዊነቷን ተዳፍረው የመጡባትን ለመመከት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ "ኢትዮጵያውያን ጦርነት ምን እንደሆነ ስለሚያውቁ ይፈሩታል፤ ይሸሹታልም፤ ገፍቶ የመጣ ካለ ግን ለሰላማቸው ሲሉ ተዋግተው ያሸንፉታል"፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተደጋጋሚ የታየው ይኸው እውነታ ነው፡፡

የጥንት ኢትዮጵያውያን ወኔ እና የሀገር ፍቅራቸው በየትኛው ደረጃ ተዘጋጅቶ የመጣን ጠላት ድል እንዲመቱ አስችሏቸዋል፡፡ በሁለቱም የጣሊያን ወረራዎች ወቅት ኢትዮጵያውያን አርበኞች ያሳዩት ወኔ የዚህ ምስክር ነው፡፡

ጠላቶቿ እንደማይተኙላት የምታውቀው ኢትዮጵያ ታዲያ ጦሯን ማዘመን ከጀመረች አንድ ምዕተ ዓመት ሆኗታል፡፡ የዛሬ 90 ዓመት ደግሞ ምድሯን ብቻ ሳይሆን ሰማይዋን የምታስከብርበት ዝግጅት እንደሚያስፈልጋት አሰበች፡፡ እናም እንደ ንስር ከፍ ብሎ እንደ አንበሳ እያጓራ ጠላት የሚያሸብር አየር ኃይል አቋቋመች፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የአፍሪካ ቀዳሚ አየር ኃይል ነው፡፡ ያኔ ገና የአፍሪካ ሀገራት እንኳን አውሮፕላን ሊኖራቸው ከቅኝ ግዛት ባልተላቀቁበት ዘመን በሩቅ አሳቢዎቹ አባቶች ነው የተጠነሰሰው፡፡ ሩቅ አስቦ የተወለደው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ጀብድ እየሠራ እነሆ 90 ዓመታት አለፉት፡፡  

የአየር ኃይሉ ምሥረታ ጥንስስ ከጣሊያን ወረራ በፊት እንደነበር ታሪኩ ያሳያል፡፡ በጣሊያን ወረራ ምክንያት የተጀመሩ ሥራዎች ለአጭር ጊዜ ቢቋረጡም የኢትዮጵያውያን የሰማይ ላይ ህልም ግን በጀግኖቹ መንፈስ ውስጥ ህያው ሆኖ ቆይቷል።

ጣሊያን ከተባረረች በኋላ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ታላቅ ራዕይ ለማሳካት ሥራዋን በፍጥነት ቀጠለች። በብሪቲሽ እና በአሜሪካ አጋሮች ድጋፍ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን እና የሥልጠና ባለሙያዎች ሥራ ጀመሩ። በ1954 ዓ.ም የኢትዮጵያ አብራሪዎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስር በመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ ተሳተፉ፡፡ ይህም አየር ኃይሉ ለዓለም አቀፍ ተልዕኮ ተሳትፎ የሚያበቃውን ሙያዊ መስፈርት ማሟላቱን ማሳያ ሆነ።

1970ዎቹ ኢትዮጵያ ከሶቭየት ኅብረት ጋር ጠንካራ ወታደራዊ ግንኙነት የመሰረተችበት ወቅት ነበር፡፡ ይህ ወቅት አየር ኃይሉ ሚግ-21 ተዋጊ ጄቶችን፣ አን-12 የትራንስፖርት አውሮፕላኖችን እና ሚ-24 ሄሊኮፕተሮችን ጨምሮ አዳዲስ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን የታጠቀበት ወቅት ነበር። በሰው ኃይልም በአውሮፕላኖችም የቀጣናው ዋና ኃይል ሆኖ የወጣው አየር ኃይሉ ከ1969 እስከ 70 በተካሄደው የኦጋዴን ጦርነት ላይ የአየር የበላይነቱን በመውሰድ ኢትዮጵያ ጦርነቱን በበላይነት እንድታጠናቅቅ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ የሶቪየት አማካሪዎች እና የኩባ የቴክኒክ ማሻሻያ ድጋፎች የኢትዮጵያ አየር ኃይል የቀጣናው አስፈሪ ኃይል እንዲሆን አስችሎታል።

ከ1983 ዓ.ም በኋላ የነበረው የመንግሥት ለውጥ አየር ኃይሉን ፈተና ውስጥ ያስገባ ነበር፡፡ በወቅቱ ሥልጣን የያዘው ኢሕአዴግ ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ጦርነት እንደማያስፈልጋት እና አየር ኃይሉም እምብዛም አስፈላጊ እንዳልሆነ የውሳኔ ሀሳብ አቀረበ፡፡ ከዚያም በላይ ተቋሙ ለዘመናት ያፈራቸው የትም የማይተኩ በርካታ ባለሙያዎች ግማሾቹ እንዲሰደዱ ሌሎቹ ደግሞ በእስር እንዲማቅቁ ተደረጉ፡፡ በመዘመን ላይ የነበረው ተቋምም አውሮፕላኖቹን ዳዋ እስኪበላቸው ድረስ ፈተና ውስጥ ገባ፡፡ በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባው አየር ኃይል ግን በተግዳሮቶች ውስጥም በቀሩት ባለራዕይ ባለሙያዎቹ ሀገራዊ ተልዕኮውን መወጣቱን ቀጠለ፡፡

የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የአየር ኃይሉ ጀብድ

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ታላቋን ሶማሊያ እመሰርታለው የሚል ሀሳብ ይ ኢትዮጵያን የወረረበት ወቅት! ኢትዮጵያ በአንጻሩ አንድም የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች የሚጋሯቸው እሴት ስላሉ ጦር የሚያማዝዝ ጉዳይ የለም ብላ፣ በሌላ በኩል በውስጥ ጉዳይዋ ተጠምዳ የነበረችበት ወቅት! ያኔ ለጦርነት በብዙ የተዘጋጀችው የዚያድ ባሬዋ ሶማሊያ ያለከልካይ በምሥራቅ እስከ 700 ኪሎ ሜትር በደቡብ ምሥራቅ እስከ 300 ኪሎ ሜትር ገብታ የኢትዮጵያን ግዛት በኃይል ያዘች፡፡

የሰውን የማትፈልገው ነገር ግን ፈልገው ሲመጡባት በነጻነቷ የማትደራደረዋ ኢትዮጵያ ልጆቿን ተጣራች፡፡ ልጆቿም መከፋቷን ዐይተው መደፈሯ አንገብግቧቸው በአንድነት ሆ ብለው ተነሱ፡፡ የወራሪውን የመስፋፋት ከንቱ ቅዠትም አየር ላይ በተኑት፡፡ በሰው ኃይልም ሆነ በትጥቅ ለረጅም ጊዜ ዝግጅት በማድረግ ኢትዮጵያን የወረረውን የዚያድ ባሬን ኃይል ለማሸነፍ የአየር ኃይል ሚና እጅግ የላቀ ነበረ፡፡ በጥቂት የውጊያ አውሮፕላኖች ነገር ግን የአባቶቻቸውን ወኔ ከልዩ ብቃት ጋር ያጣመሩ የሰማይ አንበሶች ለወራሪው የራስ ምታት ሆኑ፡፡

ኦስትሪያዊው የጦር ተንታኝ እና የታሪክ ተመራማሪ ቶም ኩፐር "Wings over Ogaden: the Ethiopian-Somali war, 1978-79" በሚለው መጽሐፋቸው የወራሪውን ህልም መና ያስቀረውን የአየር ኃይሉ ሚና እና የአብራሪዎቹን ጀግንነት በዝርዝር አቅርበዋል።

ኤርትራ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜም የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት በመወጣት የሰባት ዓመት ዝግጅቷን ከንቱ አድርጓል፡፡

አየር ኃይል ዛሬ

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዛሬም ለወገኖቹ መከታ፣ ኢትዮጵያን በክፉ ለሚያስቡአት ደግሞ የቀን ቅዠት ነው፡፡ "ሰማዩ የእኛ ነው!" የሚለው የኢትዮጵያ አየር ኃይል እንደ መሪ ቃሉ የኢትዮጵያን የአየር ክልል በአስተማማኝነት እየጠበቀ ይገኛል፡፡

ራሱም እያመረተ ጭምር ዘመኑ ያፈራቸው ትጥቆች ባለቤት የሆነው አየር ኃይሉ ማንኛውንም ትንኮሳ የሚመክት እና የኢትዮጵያ ጠላቶች ደጋግመው እንዲያስቡበት በሚያደርግ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ምናልባትም አየር ኃይሉ በአስተማማኝ ቁመና ላይ ባይሆን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በየቀኑ የሚፎክሩትን ተግባራዊ እንዳያደርጉት የሚያግዳቸው ምንም ነገር አይኖርም ነበር፡፡

የ2010 ዓ.ም ለውጥ ሪፎርም ትኩረት ማዕከል ከሆኑ ተቋማት መካከል አንዱ አየር ኃይሉ ነው፡፡ በሪፎርሙም ተቋሙ ኢትዮጵያን የሚመጥን እንዲሆን ስትራቴጂ ተነድፎ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ በስትራቴጂው መሰረትም ተቋማዊ አቅሙ የላቀ እንዲሆን ያሉትን አውሮፕላኖች በተሟላ አቅም ወደ ሥራ ከማስገባት በተጨማሪ የዘመኑን ቴክኖሎጂ እንዲታጠቅ ተደርጓል፡፡ 

አየር ኃይሉ በጦርነት ወቅት ማሸነፍ እና ማውደም የሚችል ስትራቴጂክ አቅም በመፍጠር ረገድ አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግቧል። ባነሰ ኪሳራ ከፍተኛ ድል ሊያስመዘግቡ የሚችሉ ዘመኑ ያፈራቸውን መሣሪያዎች የታጠቀው አየር ኃይሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ጉዳይ ገብተው ለመፈትፈት ለሞከሩት ተግባራዊ ምላሽ የሰጠው በቅርቡ ነው፡፡

አስተማማኝ የደኅንነት ዋስትናነቱ ደግሞ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድም ጭምር መሆኑን አልሸባብ እንደልቡ እንዳይስፋፋ ነበልባላዊ ምቱን እያሳረፈበት ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባይኖር አልሸባብ ምናልባትም ከአፍሪካ ቀንድም አልፎ ለአፍሪካ ጭምር አደጋ የሚፈጥር አሸባሪ ድርጅት በሆነ ነበር፡፡ አየር ኃይሉ በምሥራቅ አፍሪካ እና በመላው አፍሪካ ሰላምን በማስከበርም ዝናን ያተረፈ የኢትዮጵያ መከታ ነው፡፡  

በአስቸጋሪ ወቅት እና ጊዜ ሁሉ የሀገሩን የአየር ክልል የሚጠብቁ እና ጠላትን በአየር ላይ ማስቀረት የሚችሉ የአባቶቻቸው ወኔ ወራሽ የሆኑ አብራሪዎችን እና ሙያተኛን አደራጅቶ መዘመኑን ቀጥሏል።

ለፈተናዎች ሳይበገር 90 ዓመታትን ለኢትዮጵያ መከታ፣ በከፉ ለሚያስቧት ደግሞ አስፈሪ የሆነው የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመቱን የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ የነፃነትና የአንድነት ምልክት” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ሁነቶች ያከብራል፡፡

በተለይም ከተለያዩ አጋር ሀገራት ጋር በመተባበር “የአንበሶች ሰማይ፣ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል የሚያካሄደው የአየር ትርዒት በጉጉት እየተጠበቀ ነው፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች፣ የሩስያ፣ የሞሮኮ እና የቼክ ሪፐብሊክ አየር ኃይሎች ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ጋራ በመሆን የአየር ትርዒቱን የሚያቀርቡ ይሆናል፡፡

 

በለሚ ታደሰ