ኢትዮጵያ ስትፈጠር ጀምሮ ከባሕር በር ጋር ስለመፈጠሯ ምስክር የማያስፍልገው ፀሐይ የሞቀው እውነት እንደሆነ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ዓለም የሚያውቀው ሐቅ ነው።
በመከላከያ ሚኒስቴር የውጪ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ እንዲህ ያለውን እውነት ሁሉም ዜጋ መገንዘብ ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ከባሕር በር ጋር ተፈጥረን የኖርን መሆናችንን በዓለም መድረክ አሳማኝ ማስረጃ አቅርበን የምናሸንፍበት ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እውነታውን ሊያውቀው ይገባል ነው ያሉት፡፡
ታሪካዊ ጠላቶቻችን ባንዳዎችን በመጠቀም፣ የህልውናችን፤ የእስትንፋሳችን፤ የወደፊት የኢትዮጵያን ጉዞ የሚወስነውን ትልቅ ጉዳይ የሆነውን ባሕር በር አሳልፈው እንደሰጡ ማወቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል ጄነራሉ፡፡
ላለፉት 3 አስርት ዓመታት የባሕር በር አጥተን በመቆየታችን እንደ ሀገር በኢኮኖሚ ተጎድተናል፤ የሰላምና ፀጥታ ተጋላጭነታችንን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሰፋ አድርጎታል ብለዋል፡፡
አሁን የባሕር በር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ አጀንዳዎች አንዱ መሆኑን የተናገሩት ጄነራሉ፣ ማንኛውም አካል ሌሎች ጉዳዮችን ከዚህ አጀንዳ ጋር እየለጠፈ ሊያደናግረን ቢሞክርም ጉዳዩ የብሔራዊ አጀንዳ ጉዳይ ነው ብለን ልንሞግት ይገባል ሲሉም ነው የተናገሩት።
የባሕር በር ጉዳይ የአርሶ አደሩ፣ ነጋዴው፣ ወጣቱ ተማሪ ሁሉም ጋር የሚገባ በመሆኑ ብሔራዊ አጀንዳነቱ በመገንዘብ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በታሪካዊ ጠላቶቻችን ሴራ ያጣነውን የባሕር በር ለማስመለስ የአሁኑ ትውልድ ራሱን ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ እንዲያደርግ ሜጀር ጄነራል ተሾመ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በላሉ ኢታላ