Search

የዘመናዊ አውሮፕላኖች የቀለም ቅብ እና ቅየራ ጥበብ

ዓርብ ጥር 01, 2018 76

በአሁኑ ወቅት ኤርባስ ፣ ቦይንግና የተለያዩ ኩባንያዎች የሚያመርቷቸው ዘመናዊ ግዙፍ አውሮፕላኖች ውጫዊ አካላት ከ50 በመቶው በላይ የሚገነቡት ከአሉሚኒየም ሳይሆን ከካርቦን ፋይበር ነው።
በዚህም ምክንያት የዘመናዊ አውሮፕላኖችን ቀለም መቀየር ሲያስፈልግ፣ እንደ ቀድሞዎቹ አውሮፕላኖች በኬሚካል ማስለቀቅ አይቻልም።
ኬሚካሉ የአውሮፕላኑን አካል ሊጎዳ ስለሚችል፣ የቀድሞውን ቀለም ለማስለቀቅ የተለየ ጥንቃቄን ይጠይቃል።
የዘመናዊ አውሮፕላኖችን የቀለም ቅብ ሥራ ፈታኝ የሚያደርገውም ቀድሞ የነበረውን ቀለም ያለ ኬሚካል እርዳታ ማስለቀቅ በሚችል ማሽን (Sanding) አማካኝነት በከፍተኛ ጥንቃቄ ስለሚሠራ ጭምር ነው።
በርካታ አየር መንገዶችም የቀለም ቅብ ለማስቀየር ሲፈልጉ አውሮፕላናቸውን ወደ አሜሪካ እና ፈረንሳይ እንዲሁም ወደ ቻይና በመውሰድ የሚፈልጉትን አይነት መልክ እንዲይዝ ያደርጋሉ።
ይህ ሒደት ደግሞ ለተጨማሪ ነዳጅ እና ለተለያዩ ወጪዎች የሚዳርግ በመሆኑ ተመራጭ አይደለም።
 
አቅሙን በየጊዜው እያጎለበተ የሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን ጥገና ክፍል፣ በዚህ ረገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የአውሮፕላን ሙሉ የቀለም ቅየራና የቅብ ሥራ በሁለት የA350-900 አውሮፕላኖች ላይ በተሳካ ሁኔታ ማከናወኑ አይዘነጋም።
ከዚህ ቀደም የዘመናዊ አውሮፕላኖችን የቀድሞ ቀለም የማስለቀቅና አዲስ የመቀባት ሥራውን ለማከናወን ወደ አውሮፓ በሚደረግ ጉዞ ይባክን የነበረውን ነዳጅና የተለያዩ ወጪዎች በማስቀረትም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን ማዳን ያስቻለ ሥራ ተከናውኗል።
አሁን ላይ አየር መንገዱ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በራሱ ባለሙያዎች፣ በዓለም እጅግ ዘመናዊ የሚባሉትን ‘ኤችቪኤልፒ (HVLP) እና ኤሌክትሮስታቲክ (Electrostatic)’ የተሰኙ የቀለም አረጫጭ (ስፕሬይ) ዘዴዎችን በመጠቀም ሥራውን በሀገር ውስጥ ማከናወን ጀምሯል።
ይህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬን ከማዳን ባለፈ፣ አገልግሎቱን ለሌሎች ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች በመስጠት ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንደሚያስገኝ ተገልጿል።
አየር መንገዱ በቅርቡ 150 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገባቸውን ዘመናዊ የጥገና ተቋማት፣ የመለዋወጫ መጋዘን እና ወርክሾፖችን መክፈቱ ይታወሳል።
 
በዋሲሁን ተስፋዬ