አንድ የንግድ አውሮፕላን የአገልግሎት ዘመን ከ20 አስከ 30 እንደሆነ የአቪየሽን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የተጠቀሰው የአገልግሎት ዘመን እንዳለ ሆኖ የአውሮፕላኖቹ የበረራ ድግግሞሽ፣ የበረራ ሰዓት እና የቴክኖሎጂ ተለዋዋጭነት የአውሮፕላኖችን የአገልግሎት ዘመን ከሚወስኑት መካከል ናቸው፡፡
በአቪየሽን ኢንዱስትሪው የአውሮፕላን የገልግሎት ዘመን የአየር መንገዶችን ተወዳዳሪነት ከሚወስኑት መካከል ናቸው፡፡ አዳዲስ አውሮፕላኖች የደንበኞች ምቾት በመጨመር፣ በነዳጅ ቁጣባ፣ የጥገና ወጪን በመቀነስ እና የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ባለቤት በመሆን ለአየር መንገዶች ተወዳዳሪነት አቅም ይሆናሉ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዳዲስ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ግንባር ቀደም ከሆኑ አየር መንገዶች አንዱ ነው፡፡ አየር መንገዱ በአፍሪካ አማካኝ የአገልግሎት ዘመናቸው ከ7 ዓመት በታች የሆናቸው በርካታ አውሮፕላኖች ባለቤት ነው።
ከ167 በላይ በሆኑት አውሮፕላኖቹ ከ145 በላይ መዳረሻዎችን የሚያካልለው አየር መንገዱ "ራዕይ 2035" ለማሳካት ከ100 በላይ ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ለመጨመር ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ከአየር መንገዱ የስኬቱ ምስጢሮች መካከል በአቪየሽን ኢንዱስትሪው የመጨረሻ ቴክኖሎጂ የሆኑ አዳዲስ አውሮፕላኖች ባለቤት መሆኑ ነው፡፡ "እጅግ ዘመናዊ" ከሚባሉት አውሮፕላኖች መካከልም እንደ ኤርባስ A350፣ ቦይንግ 787 ድሪምላይነር እና ቦይንግ 737 ማክስ ያሉ ነዳጅ ቆጣቢ አውሮፕላኖችን በእጁ ለማስገባት የቀደመው የለም።
አየር መንገዱ ኤርባስ A350 እና ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላኖች ባለቤት ለመሆን በአፍሪካ ቀዳሚው ነው። እነዚህ አውሮፕላኖች የአየር መንገዱ ከፍተኛ ተፎካካሪዎች ወዳሉባቸው መካከለኛ ምሥራቅ፣ አሜሪካ፣ አውሮፓ እና እስያ የሚያደርጋቸውን ጉዞዎች ቀና አድረገውለታል።

ኤርባስ A350-1000 እጅግ ዘመናዊ እና ግዙፍ ከሆኑት አውሮፕላኖች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዚህ አውሮፕላን ባለቤት በመሆን ከአፍሪካ ቀዳሚ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን ቀድሞ የአውሮፕላኑ ባለቤት የሆኑት ግዙፎቹ የአውሮፓ እና መካከለኛ ምሥራቅ አየር መንገዶች ብቻ ናቸው፡፡ አየር መንገዱ በአሁኑ ጊዜ አራት ኤርባስ A350-1000 አውሮፕላኖች ባለቤት ነው፡፡
ሌላው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በእጁ ያለው እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላን ኤርባስ A350-900 ነው፡፡ 22 ኤርባስ A350-900 ያሉት ሲሆን፣ 11 ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግንባር ቀደም የቦይንግ ደንበኛ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አዳዲስ እና ዘመናዊ የቦይንግ ምርቶችን በእጁ ለማስገባት የሚቀድመው የለም፡፡ ከቦይንግ ምርቶች መካከልም እጅግ ምቹ እና ፈጣን የሆኑት ቦይንግ 787-9 ድሪምላይነር እና ቦይንግ 787-8 ዲሪምላይነር አውሮፕላኖችን የራሱ በማድረግ ቀዳሚው አየር መንገድ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ 10 ቦይንግ 787-9 ዲሪምላይነር ባለቤት ሲሆን፣ 11 አውሮፕላኖችን ለመጨመር ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ 19 ቦይንግ 787-8 ድሪምላይነር አውሮፕላኖችም አሉት፡፡

ከዘመናዊ የቦይንግ አውሮፕላኖች መካከል በረጅም ጉዞዎች ላይ ባላቸው ምቾት የሚታወቁት ቦይንግ 777-300ER እና 777-200LR በአየር መንገዱ እጅ የሚገኙ ናቸው፡፡
አየር መንገዱ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚያደርጋቸው በረራዎቹ ዘመናዊ የሆኑ የቦይንግ አውሮፕላኖችን ይጠቀማል። 27 ቦይንግ 737 MAX 8 አገልግሎት አየሰጡ ሲሆን፣ ተጨማሪ 34 አውሮፕላኖችን አዝዞ እየተጠባበቀ ነው።
የኢትዮጵያ ካርጎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕቃዎችን በማንቀሳቀስ በዓለም ላይ ካሉት ትልቁ ኩባንያዎች አንዱ ነው። የአየር መንገዱ ካርጎ በርካታ አየር መንገዶች ገበያ ውስጥ ለመቆየት ድጎማ ባስፈለጋቸው የኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ደኅንነቱን የጠበቀ የጭነት አገልግሎት ከአፍሪካ እስከ ላቲን አሜሪካ በማድረስ ህይወት አድን መሆኑን ያስመሰከረ ነው፡፡
የጭነት አገልግሎቱንም 12 ቦይንግ 777-200LRF፣ 4 ቦይንግ 767-300F እና 4 ቦይንግ 737-800F አውሮፕላኖች በትጋት እያቀላጠፉት ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሰፊ ተደራሽነቱ እና አዳዲስ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ስትራቴጂው ይታወቃል። አዳዲስ አውሮፕላኖችን መጠቀሙ ተወዳዳሪነቱን ከማሳደጉም በተጨማሪ ከ20-25 እስከ የነዳጅ ወጪዎች ይቆጥብለታል፡፡ ይህም የካርቦን ልቀትን በእጅጉ በመቀነስ ኢትዮጵያ ከተያያዘችው የአረንጓዴ ልማት ጋር በእጅጉ የሚናበብ ነው።

አየር መንገዱ አገልግሎቱን በማዘመን ከፍታው ላይ ለመቆየት የሚያስችለውን አዲስ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ አስጀምሯል፡፡ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት አዲሱ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ አየር መንገዱን ወደ አዲስ የከፍታ ምዕራፍ የሚያደርሰው ነው፡፡
ከጉባ ብሥራቶች አንዱ የሆነው የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊ በዓለም ላይ ከተመዘገቡት 15 ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል ሲሆን፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቅቆ አገልግሎት ሲጀምር አሁን ያለውን 25 ሚሊዮን ዓመታዊ የተሳፋሪዎች ብዛት ወደ 60 ሚሊዮን ያሳድጋል፡፡ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት ሲጀምርም በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን እንደሚያስተናግድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል፡፡
በለሚ ታደሰ