Search

አቡሴራ ለምን ተመረጠ? ስልታዊው ውሳኔ

እሑድ ጥር 03, 2018 377

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአቪዬሽን ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በቢሾፍቱ አቡሴራ ተጀምሯል።
ይህ ፕሮጀክት በቦታ መረጣው ረገድ በርካታ ሳይንሳዊ እና ስልታዊ ምክንያቶችን መሠረት ያደረገ መሆኑም ተመላክቷል።
ተፈጥሯዊ ምቾት እና ቴክኒካዊ ብቃት
አቡሴራ የተመረጠበት ቀዳሚው ምክንያት ከባሕር ጠለል በላይ ያለው ከፍታ ነው። ቦታው በ1 ሺ 910 ሜትር ከፍታ ላይ መገኘቱ ለአውሮፕላኖች በረራ እጅግ ተስማሚ ያደርገዋል።
ይህም አውሮፕላኖች ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አንጻር ዝቅ ባለ ከፍታ ላይ እንዲንቀሳቀሱ ስለሚያደርግ፣ በከፍተኛ የጭነት አቅም (Payload) ለመነሳት እና ነዳጅ ለመቆጠብ ያስችላል።
ለተጨማሪ ኢንቨስትመንት
አካባቢው ሰፊ እና ሜዳማ መልክዓ ምድር ያለው በመሆኑ፣ ለአራት ትይዩ የመሮጫ መንገዶች (Runways) ግንባታ እና ለወደፊት ግዙፍ የአቪዬሽን ከተማ ማስፋፊያ እጅግ አመቺ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉትም፣ የአቡሴራ ፕሮጀክት ተራ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ አይደለም።
ይልቁንም ኢትዮጵያን የወደፊቷ የአፍሪካ እና የዓለም ዋነኛ የአየር ትራንስፖርት በር የሚያደርግ፣ በቢሾፍቱ ዙሪያ አዳዲስ የኢኮኖሚ ዕድሎችን የሚፈጥር እና የሀገርን ገጽታ የሚቀይር ግዙፍ የልማት አርማ ነው።
 
 
ስልታዊ ቅርበት
የአቡሴራ መገኛ ከአዲስ አበባ በ40 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ብቻ መሆኑ ሌላው ወሳኝ ነጥብ ነው።
ይህም አዲሱ ማረፊያ ከፍጥነት መንገድ እና ከዘመናዊ የባቡር መስመር ጋር በቀላሉ እንዲዋሃድ በማድረግ፣ ለተሳፋሪዎች እና ለጭነት ትራንስፖርት ቀልጣፋ ግንኙነትን ይፈጥራል።
 
ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ይህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን ከአፍሪካ አልፎ የዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ዋነኛ ማዕከል የሚያደርግ የብልፅግና ተምሳሌት መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፅንኦት እንደሰጡት፣ አውሮፕላን ማረፊያው የኢትዮጵያ አየር መንገድን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያረጋግጥ እና የአፍሪካን ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ትሥሥር የሚያቀላጥፍ ግዙፍ ሞተር ሆኖ ያገለግላል።
ይህ ስልታዊ ውሳኔ ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ ያላትን መሪነት ለቀጣይ ትውልድ የምታስረክብበት ታሪካዊ እርምጃ ነው።
 
በጌትነት ተስፋማርያም