በአውሮፓውያኑ 1956 በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ ጆን ማካርቲ የተባሉ ተመራማሪ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ሀሳብ ለዓለም አስተዋወቁ፡፡
በወቅቱ እንደ አንድ የቴክኖሎጂ ውጤት ብቻ እንጂ በጥቂት አሥርት ዓመታት ውስጥ የዓለም መነጋገሪያ ብሎም ዓለም ሁሉ የሚረባረብበት ይሆናል የሚል ብዙ ግምት አልነበረም።
ይሁን እንጂ ላለፉት 70 ዓመታት ሰው ሰራሽ አስተውሎት ከጊዜው ጋር በመዘመን አበርክቶው እየተራቀቀ እና እየዘመነ የኣለም ዋናው የትኩረት ነጥብ እየሆነ መጥቷል፡፡
በኢትዮጵያ የመደመር መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን በመመስረት ባለፉት ስድስት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች እየተተገበረ ይገኛል፡፡
የሰው ሰራሽ አስተውሎት በኢትዮጵያ አጠቃቀሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ እና በተለያዩ ቁልፍ ዘርፎች ላይ ተጨባጭ ለውጦችን ማምጣት ጀምሯል፡፡
በጤናው ዘርፍ የምርመራ ትክክለኝነትን እና ፍጥነትን ለማምጣት ብሎም አንዳንድ ወሳኝ የባለሙያ እጥረትን ለመቅረፍ ጭምር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
በግብርናው ዘርፍ ላይ የአፈርን ለምነት እና የሚፈልገውን የማዳበሪያ መጠን በቴክኖሎጂ በመለካት፣ ለአየር ትንበያ እና የሰብልን በሸታ በመለየት መፍትሔ ለመስጠት ያግዛል፡፡
በትምህርት ዘርፍ ደግሞ ለተማሪዎች የሚመጥን ትምህርት አሰጣጥ ዘዴን በመቀየስ እንዲሁም በባንክ እና የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎታቸውን ለማዘመን እየተገበሩት ይገኛሉ፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርማቲክስ ፋካልቲ ዲን ተገኝ ጎበና ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች መተግበሩ ከዚህ ቀደም አዳጋች የነበሩ ጉዳዮችን በቀላሉ እና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ተደራሽ ማድረግ አስችሏል ብለዋል፡፡
አቶ ጎበና እንዳሉት ኢትዮጵያ ወደ ዘርፉ መቀላቀሏ በሌሎች ሀገሮች የታየው የኢኮኖሚ መሻሻል እና የቴክኖሎጂ መነቃቃትን እየተቀላቀለች እንደምትገኝ አንስተው ትክክለኛ መረጃን በወቅቱ ለማግኘትም ሰፊ አበርክቶ እንዳለው አክለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ተግባራዊ ማድረጓ በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘውን የለውጥ ሒደት የመደግፍ እና እንደ ትልቅ ጀርባ አጥንት በመሆን የሚያገለግል ዘርፍ እየሆነም መጥቷል፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ