አዲስ አበባ ስሟና ግብሯ ተለያይተው ለዘመናት ኖረዋል። 76 ወንዞች ያሏት መዲናዋ ወንዞቿ ግን የውበት ሳይሆን የብክለት፣ የሕይወት ሳይሆን የበሽታ፣ የሰላም ሳይሆን የወንጀል መሸሸጊያ ሆነው ቆይተዋል።
ዛሬ ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ኃሳብ አመንጪነትና ክትትል ከተማዋ አጥታው የነበረውን የተፈጥሮ ጸጋ በኮሪደርና በወንዝ ዳርቻ ልማት አማካኝነት ዳግም እያገኘች ነው።
ትናንት በአጠገቡ ለማለፍ የሚቀፍ ቦታ ዛሬ ብዙ ሰዓታትን ለማሳለፍ የሚመርጡት ወደመሆን ሲቀየር ይህ ለውጥ እንዴት መጣ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።
የዛሬውን ለውጥ ለመረዳት የትናንቱን ሰቀቀን ማስታወስ ይገባል፤ ነዋሪዎች እንደሚመሰክሩት፣ ወንዞቹ “ሽንት ቤትና የቆሻሻ ገንዳ” ሆነው ነበር። ሽታው መተንፈስ የሚከለክል፣ ገጽታው ዐይን የሚያስነውር፣ ለጤና ጠንቅና ለወንጀለኞች መደበቂያ የነበረበት ያ ዘመን ዛሬ በታሪክ ተተክቷል።
የተፈጥሮ ጥበቃ ባለሙያው አቶ ሙሉጌታ ወርቁ እንደሚሉት፣ “ሰው ከተፈጥሮ ጋር ተጣልቶ የኖረበት” ያ አሳዛኝ ምዕራፍ አሁን አብቅቷል።
ዛሬ የቀበና እና ጊንፍሌ ድንቅ ስራዎች የትላንት መከራን ተሻግረው በኮሪደር ልማቱ የታቀፈው የወንዝ ዳርቻ ግንባታ፣ አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ አድርጓታል። የቀበና እና የጊንፍሌ ወንዞች ዛሬ በባህላዊ አባባል “የሰማይና የምድር ያክል” ለውጥ አሳይተዋል።
ይህ በመሆኑ ታዲያ የተፈጥሮ ትንሳኤ ሆኗል። የደረቁ ምንጮች መፍለቅ ጀምረዋል። አፈር እንዳይሸረሸር የተሰሩት እርከኖችና የተተከሉት አገር በቀል ዛፎች የከተማዋን “ሳንባ” እያደሱት ነው።
ዘመናዊ መሠረተ-ልማት የታየባቸውም ሆነዋል። በከተማ መሃል አይታሰብ የነበረው “ታላቁ የቀበና ግድብ”፣ ዘመናዊ የኮንክሪት፣ የብረትና የተንጠልጣይ ድልድዮች፣ እንዲሁም የብስክሌትና የእግረኛ መንገዶች ከተማዋን እንደ ዱባይና ኳታር ውብ አድርገዋታል።
ይህ ብቻም አይደለም የነገው ሀገር ተረካቢ ህፃናት በከተማዋ ታሪክ እያወቁ ነገን እያለሙ የሚጫወቱበት ስፍራ አግኝተዋል።
ይህ ልማት ውበት ብቻ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ ብሔራዊ ጥቅሞችን ይዞ መጥቷል። ወንዞቹ አሁን የቱሪስት መስህብና የሥራ ዕድል ፈጣሪ ሆነዋል።
ቀደም ሲል ሰዎች የሚዘረፉባቸውና የሚደበደቡባቸው ጨለማ ስፍራዎች ዛሬ በብርሃን ደምቀው ለ24 ሰዓት እንቅስቃሴ ክፍት ሆነዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ “ይህ ሥራ ስለ ትውልድ ማሰብ ነው፤ አፈርን መጠበቅ ትውልድ የሚበላበትን መሬት መጠበቅ ነው” የሚለውን በተግባር ያረጋገጠ ሥራ ሆኗ።
በሀገር በቀል አማካሪዎችና ኮንትራክተሮች የተከናወነው የ45 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ ልማት የኢትዮጵያ አዲስ ከፍታ ማሳያ ሆኗል።
በሰለሞን ገዳ