Search

ከአዲስ አበባ ጋር የተለወጡት የአዲስ አበባ ወንዞች

ዓርብ ጥር 08, 2018 281

አዲስ አበባ 76 ወንዞች እና ጅረቶች መገኛ እንደሆነች መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ እንጦጦ ተራራ ስር እንደመመስረቷ ከእንጦጦ የሚመነጩ ወንዞች የከተማዋ በረከቶች ነበሩ፡፡

ድሮ ድሮ እነዚህ ወንዞች በርካቶች የሚዋኙበት ንፁህ እና ማራኪ ነበሩ፡፡ ዳሩ አዲስ አበባ እያደገች ስትሄድ ወንዞቿን ረሳቻቸው እንጂ

የቆዳ እና ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ሲቋቋሙ እነዚያን በርካቶች ዋኝተው ያደጉባቸው ወንዞችን ትዝታ ብቻ ሆነው ቀሩ፡፡ ፋብሪካዎች ሲቋቋሙ እና መኖሪያ ቤቶች ሲሠሩ ከእነዚ ለሚወጡ ፍሳሾች መፍትሔ አልተበጀም፡፡ ይባስ ብሎም በመኖሪያ ቤት እጥረት ምክንያት የተቸገሩ ወገኖች ሸራ ዘርግተው የወንዞቹ ዳርቻዎች ላይ ሰፈሩ፡፡ 

እናም ለብዙዎች የሕይወት ምንጭ የነበሩት የአዲስ አበባ ወንዞች መከኑ፡፡ መክነው መቅረት ብቻ ሳይሆን በየክረምቱ የበርካቶችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ ሆነው ቀጠሉ፡፡

ወንዞቹ የሚያበቅሉአቸውን አትክልቶችን መብላት የዘላቂ ጤና ቀውስ ምክንያት መሆናቸው በጥናቶች ተመላከተ፡፡ ብዙዎችም አዲስ አበባ ወንዞቿን የገደለች ቆሻሻ ከተማ እስከማለት ደረሱ፡፡

እስከቅርብ ዓመታት ድረስ የአዲስ አበባ ወንዞች ከፋብሪካዎች የሚወጡ እና ከየቤቱ የሚለቀቀሱ ፈሳሾችን ተሸክመው የሚጓዙ የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች ሆነው ቀጥለው ነበር፡፡

እንጦጦ ከምንጮቿ የሚወጣ ንፁህ ውኃዋን ማበርከቷን ባታቆምም አዲስ አበባ ውኃውን የመጣላት የንፁህ ምንጭ ውኃ ማባከንን ልማዷ አድርጋ ነበር፡፡

ተመራማሪዎች እየመጣ ያለውን ጥፋት አመላክተው አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ቢጮሁም ሰሚ አላገኙም፡፡ በተለይም ከፋብሪካዎች እና ከሆቴሎች የሚወጡ ፍሳሾች በወንዞች ዳር የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ላይ ያደረሱት ጉዳት በግልፅ ቢታይም ጉዳዩን ከቁብ የቆጠረው ግን አልነበረም፡፡

ወደ አዲስ አበባ አረንጓዴ ሳንባነት የተቀየሩት የአዲስ አበባ ወንዞች

የኮሪደር ልማት ይዞት በመጣው ከተሞችን የማዘመን እሳቤ መሰረት 47 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ፕሮጀክቱ ስምንት ዋና ዋና የውኃ መስመሮችን ወደ ቀድሞ የተፈጥሮ ንጹህ ይዘታቸው በመመለስ ዳርቻዎቹን ማዘመን ላይ ያተኮረ ነው።

2019 የተጀመረው "ሸገርን ማስዋብ" ፕሮጀክት የወንዞችን ሥነ-ምህዳሮች በመሠረታዊነት ለውጧል፡፡ የወንዝ ዳር ልማት አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስ እንድትሆን አድርጎታል፡፡ በዚህም ምክንያት አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ጤናማ ከመሆን አልፋ ብዙዎች ሊገበኟት የሚመኟት ውብ ከተማ ሆናለች፡፡

90 በመቶ በላይ ፍሳሽ ማስወገጃዎች የነበሩት የአዲስ አበባ ወንዞች አሁን የፍሳሽ ማሰወገጃ እና ማከሚያ ተሠርቶላቸው ኩልል ያለ ውኃ መገኛ ሆነዋል።

በአረም እና በግንባታ ተረፈ ምርቶች የተደፈኑት ወንዞች አሁን ንጹህ እና ዳርቻዎቻቸው በሀገር በቀል ዛፎች ተሸፍነው የአዛውንቶች ማረፊያ እየሆኑ ናቸው፡፡

አደገኛ፣ ለወንጀል የተጋለጡ፣ ለጎርፍ ምክንያት የነበሩት እና ማንም ሊሄድባቸው የማይፈልጉት ወንዞች አሁን የሳይክል መንገድ እና የስፖርት ማዘውተሪያዎች የተሠሩላቸው እና በርካቶች የዕረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉባቸው ውብ ቦታዎች ሆነዋል፡፡

ከመበከላቸው የተነሳ የከተማዋን ሙቀት ከፍ እያደረጉ የነበሩት ወንዞች ዛሬ ተጨማሪ ሰው ሠራሽ ሐይቆች ጭምር ተሠርቶላቸው የከተማዋ ንፁህ አየር ምንጭ እየሆኑ ናቸው፡፡

ከእንጦጦ-ፒኮክ ኮሪደር ያለው እና የእንጦጦ የውኃ ምንጭን ከመሀል ከተማ ጋር የሚያገናኘ 21 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የወንዝ ዳርቻ የአዲስ አበባ "አረንጓዴ ሳንባ" እየሆነ ይገኛል።

ከእንጦጦ ተነስቶ በቀበና ወንዝ እስከ ካራማራ ድልድይ ድረስ 19 . የሚዘረጋው ወንዝ ጸድቶ ዳርቻውም ለሰዎች እግር ጉዞ እና ማረፊያ በሚሆን መልኩ ተዘጋጅቷል።

ግንፊሌ ወንዝ እጅግ ከተጎሳቆለበት ይዞታው ወደ ንፁህ እና አረንጓዴ ኮሪደር ተቀይሮ ከዘመናዊ የእግረኛ መንገዶች ጋር ታድሷል።

የከተማዋን ውኃ በማሰባሰብ አቃቂ-ቃሊቲ በኩል ወደ አባ ሳሙኤል ግድብ የሚወስዱ ዋና ዋና ተፋሰሶች ለምተው ለጤናም ለዓይንም ተስማሚ ሆነዋል፡፡

በባህል በበለጸጉት ፒያሳ እና ሽሮሜዳ አካባቢዎች የሚያልፈው የቀጨኔ ወንዝ ለአካባቢዎቹ ውበትን መጨመር ብቻ ሳይሆን የጤና ምንጭም በሚሆንበት መልኩ ለምቷል።

የቡልቡላ እና ሃርቡ ወንዞች የኮርደር ልማቱ አካል በሆነው የወንዝ ዳርቻ ልማት አካል ሆነው ውበታቸው ጨምሯል፤ ቀድሞ የደረቁ ምንጮቻቸውም እየተመለሱ ነው።

 

በለሚ ታደሰ