Search

የለውጥ ሥራ እንዲስፋፋ ሁሉም የየድርሻውን ሊወጣ ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ቅዳሜ ጥር 09, 2018 205

የገጠር ኮሪደር የአርሶ አደሮችን እና አርብቶ አደሮችን ሕይወት በመለወጥ ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወት ሀገራዊ ሥራ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ዛሬ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጉራፈርዳ ወረዳ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እና ተጠሪ ተቋማት የተሰሩትን የሞዴል ገጠር ኮሪደር ስፍራ ጎብኝተናል ብለዋል።
ሞዴል ሥራው እያንዳንዳቸው ሳሎን፣ መኝታ ቤቶች፣ የእንስሳት ክፍል እና የውጭ መጸዳጃ ክፍሎች ያላቸው አስር ዘመናዊ ቤቶችን ያካተተ መሆኑን አስታውቀዋል።
ቤቶቹ ከኤሌክትሪክ መስመር ጋር የተገናኙና የሳተላይት ዲሽ የተገጠመላቸው ናቸው ሲሉ በማኅበራዊ የትስስር ገፅ አስፍረዋል።
በተጨማሪም ጊቢው የዶሮ ማርቢያዎች፣ የእንስሳት በረት፣ የንብ ቀፎዎች ብሎም በፍራፍሬ እና አትክልት የተሞሉ ጓሮዎች አሉት ብለዋል።
የፀሐይ ኃይልን፣ ባዮጋዝ እና ሌሎች የልማት ሥራዎችን በመጠቀም ተቀናጅቶ የተተገበረው የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ ለማኅበረሰቡ ዘመናዊ፣ ጤናማ፣ ጽዱ እና ለተሻሻለ የአኗኗር ዘይቤ ጠንካራ እድል የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይኽ የለውጥ ሥራ በሁሉም ዘርፍ ረገድ እንዲስፋፋ ሁሉም የየድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።