የጎንደር የቅርስ ጥበቃና የልማት ስኬቶች የከተማዋን ገናና የሥልጣኔ ዘመን ዳግም ያበሰሩ መሆናቸውን ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።
ለጎንደር ከተማ ማንሠራራት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት "ጎንደር ታመሰግናለች" የተሰኘ የምስጋና እና ዕውቅና መርሃ ግብር በዓፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥታት ቅጥር ግቢ እየተካሄደ ነው።
በመርሃ ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፤ ለጎንደር ከተማ ልማት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሁሉ የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
የጎንደር ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት ካለው ቀናኢነትና ታታሪነት ባሻገር፣ ያደረጉለትን ማመስገን ባህሉ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለዓፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥታት ዕድሳትና ለጎንደር ገናና የታሪክ ሥልጣኔ መነሳት ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
በአሁኑ ወቅት ጎንደር በትውልድ ትንሣኤ ዘመን ላይ መሆኗን ገልጸው፤ የጎንደር ገናና የሥልጣኔ ታሪክ የኪነ-ጥበብ፣ የትምህርት፣ የዕድገትና የልማት መገለጫዋ ነው ብለዋል።
ይህ እንዲሆን በጎንደር ከተማ የልማትና የቅርስ ዕድሳት ስኬት ለተጨነቁና ላሰቡ፣ በትግበራ ሂደቱና በፍጻሜው ደስታን ላገኙ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በቀጣይም የጎንደርን ዕድገትና ብልፅግና በማስቀጠል፣ በቅርስ ጥበቃና አዳዲስ ልማትን በማንበር ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው፤ ጎንደር ትሞሸር በሚል ለቀረበው ጥሪ ሁሉም በጎ ምላሽ በመስጠት ከተማዋ ውብና ምቹ እንድትሆን ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።
አሁንም ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የምንሠራው ጎንደርን ወደ ነበረችበት ሥልጣኔ ለመመለስ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የበለጠ ለማድመቅ እና ለማስፋት ጭምር ነው ብለዋል።
ጎንደር የበለጠ የኢንዱስትሪ እና የሥልጣኔ ከተማ እንድትኾን መሥራት እንደሚገባም አመላክተው፤ ጎንደርን ይበልጥ ውብ፣ ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግና የቱሪስት መዳረሻነቷን ለማጠናከር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ዳግም ጥሪ አቅርበዋል።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፤ በአሁን ወቅት የጎንደር የሥልጣኔ ዘመን በብልፅግና መንገድ እያንሠራራ ነው ብለዋል።
በጎንደር ዓፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥታት ዕድሳትና የልማት ስኬቶች ድጋፍና አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።
በዕውቅና መርሃ ግብሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እንዲሁም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።