Search

ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ፦ የትህትናው ጉዞ ብርሃን እና መገለጥ

ሰኞ ጥር 11, 2018 827

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአደባባይ ከምታከብራቸው በዓላት አንዱ የጥምቀት በዓል ነው። ይህ በዓል ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ መሠርት ያለው በመሆኑ በብዙ ምሥጢራት የተሞላ ነው።

4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የጥምቀት በዓል አሁን ባለው የአከባበር ሥርዓት ሲከበር እንደነበር የቤተ ክርስቲያን መረጃዎች ያመላክታሉ። ከአብርሃ ወአጽብሃ ዘመን ጀምሮ ይህ በዓል በተለይ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ እንደተጠበቀ እንዲቀጥል ተደርጓል።

ይህ በዓል ታቦታት ከመንበር ክብራቸው ተነሥተው ወንዝ ወይም ውኃ ባለበት ቦታ ለማደር ጉዞ ሲጀምሩ በሕዝብ ታጅበው በመሆኑ ብዙ መዝሙራት እና ምስጋናዎችም ይቀርባሉ። ይህ እንግዲህ እንደየአካባቢው ባህል እና ቋንቋ ሕዝቡም የራሱ ክዋኔዎች ያሉት በመሆኑ በዓሉ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ እና ባህላዊ ክንውኖች የሚቀርቡበት ሆኖ ይከበራል።

በእርግጥ የጥምቀት በዓል የመከበሩ ዋና አስተምህሮ የኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ በገለጠው የማዳን ሥራው፣ በሰላሳ ዘመኑ ከገሊላ ናዝሬት ተነሥቶ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ከማምራቱ ይጀምራል። ይህ ጉዞ የትህትና ጉዞ ነበር፤ ጌታ ወደ ባሪያው የመጣበት ታላቅ ምሥጢር ነው።

እንደ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ "እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል" ብሎ ሲከለክለው፣ ጌታ ግን ጽድቅን ሁሉ ለመፈጸም መጠመቅ እንደሚገባው በቃል እና በተግባር አሳየ። በገሊላ ተወልዶ ያደገው የሕይወት ራስ፣ የሰው ልጅን ከአዳም ባርነት ነፃ ለማውጣት እና በውኃ እና በመንፈስ ዳግም ለመወለድ ምሳሌ ሊሆን ወደ ዮርዳኖስ ወረደ።

በዮርዳኖስ ባሕር ላይ የተገለጠው ምሥጢረ ጥምቀት፣ የሥላሴ አንድነት እና ሦስትነት በግልጽ የታየበት የታላቅ ብርሃን በዓል መሆኑን ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች። ጌታ በዮሐንስ እጅ ሲጠመቅ፣ አብ በደመና ሆኖ "በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው" በማለት መሰከረ፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ አረፈ።

ይህ ነው እንግዲህ ጥምቀትን የመገለጥ በዓል እንዲሆን የሚያደርገው። ይህ መገለጥ ደግሞ አንዱ ምሥጢር ነው።  ይህ ምሥጢር ከምሥጢራት ሁሉ የመጀመሪያ ነው። ምሥጢር መባሉም በዓይን በሚታይ እና በጆሮ በሚሰማ አገልግሎት በዓይነ ሥጋ የማይታይና በዕዝነ ሥጋ የማይሰማ ጸጋ ስለሚገኝበት እንደሆነ የቤተከርስቲያን መምህራን ያስተምራሉ።

ይህም ይላሉ መመህራን አገልግሎቱ ሲፈጸም ይታያል፣ ይሰማል፤ ተጠማቂው ከውኃ እና ከመንፈስ ተወልዶ የልጅነት ጸጋ ሲያገኝ ግን አይታይም፣ አይሰማም። ይህ ምሥጢር የሌሎች ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን እና የመንግሥተ ሰማያት መግቢያ በር መሆኑን ነው የሚገለጹት።

በዚህም ጊዜ የሰው ልጅ የጠፋው ልጅነት ተመለሰ፤ በኃጢአት የረከሰችው ነፍስም በክርስቶስ ጥምቀት አማካኝነት የመንጻት ጸጋን አገኘች። ዮርዳኖስም የሞት እና የፍርድ ምልክት መሆኑ ቀርቶ፣ ለምእመናን ሁሉ የሕይወት እና የድኅነት ምንጭ ሆኖ በቤተክርስቲያን ታሪክ ተመዘገበበማለት ታስተምራለች ቤተክርስቲያን።

እንዲህ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ እና ባህላዊ ይዘቶችን አዋህዶ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ለኢትዮጵያ ብርቅዬ ከሚባሉ በዓላት አንዱ እና ዋናው ነው። ዓለም ይህን ሊመለከት ወደኢትዮጵያ እንዲመጣ የሚስብ ኃይል ያለው ነውና። በእርግጥ ይህን በዓል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) ታኅሣሥ 01 ቀን 2012 . በዓለም ቅርስነት መዝግቦታል።

ይህ በራሱ ትልቅ እርምጃ ቢሆንም፣ ጥምቀትን በዓለም ማስተዋወቅ እና የስበት ማዕከል እንዲሆን በማድረጉ በኩል አሁንም ብዙ ሊሠራ እንደሚገባ የሚያመላክቱ ጉዳዮች አሉ።

ኢትዮጵያ ያላትን ብዝኃ ማንነት እና ሃይማኖታዊ ጥንታዊነት በማስተሳሰር ለማሳየት ከሚያግዙ በዓላት አንዱ ጥምቀት በመሆኑ ብዙ ሊሠራበት እንደሚችል ያመላክታል።

በጥበቡ አስፋው

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #ጥምቀት #Timket