በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በምትገኘው የገጠር ከተማዋ ኢራንቡቲ፣ ጥንታዊነቱን የጠበቀው የጥምቀት በዓል በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።
ከአዲስ አበባ 146 ኪ.ሜ ላይ የምትገኘው ይህች ታሪካዊት ሥፍራ፣ 44 ታቦታት በአንድነት ወደ ባሕረ ጥምቀቱ የሚወርዱባት የታሪክ እና የእምነት አውድማ ናት።
በኢራንቡቲ የጥምቀት በዓል መከበር የጀመረው ከ624 ዓመታት በፊት በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነ ይነገራል።

በተለይም ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀበት የዮርዳኖስ ወንዝ አምሳል፤ "ዳግማዊ ዮርዳኖስ" እየተባለ በሚጠራው የሸንኮራ ወንዝ ላይ በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት በዓሉ በታላቅ ድምቀት መከበር መጀመሩን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
በዚህም ለከተራ በዓል የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች እና አዛውንቶች “ወረደ ወልድ” እያሉ ታቦታቱን በዝማሬ አጅበው፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ረጅም ርቀትን አቆራርጠው ወደ ኢራንቡቲ ባሕረ ጥምቀት ሲደርሱ፣ ያቺ ትንሿ የገጠር መንደር በሰው ማዕበል እና በቱባ ባህል ትደምቃለች።
የከተራ ዕለት 44ቱ ታቦታት ወደ ሸንኮራ ወንዝ ሲወርዱ፣ ካህናቱ በወንዙ ዳርቻ ቆመው በከበሮ እና በጸናጽል የታጀበ ረቂቅ ያሬዳዊ ዜማ ያቀርባሉ።

ይህ መንፈሳዊ ድምፅ ከወንዙ የውኃ ሞገድ ጋር ተዋህዶ በሥፍራው ለሚገኘው ምዕመን ልዩ ስሜትን ይፈጥራል።
የኢራንቡቲ ጥምቀት በኢትዮጵያ ከሚከበሩ ደማቅ የጥምቀት በዓላት መካከል የቱሪዝም መስህብ የሆነ እና ጥንታዊ እሴቱን ጠብቆ የቆየ መሆኑን የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል።
በኢራንቡቲ ከሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቱ በተጨማሪ ቀልብን የሚስበው እና በዓሉን ይበልጥ የሚያደምቀው ሌላኛው ትውፊት የምንጃር ባህላዊ ጭፈራ ነው።
የአካባቢው ወጣቶች ሃይማኖታዊ ሥርዓት ከሚከበርባቸው ሥፍራዎች ራቅ ብለው "ሆሆ ሙና" እየተባለ በሚጠራው የምንጃር ባህላዊ ጭፈራ ወግ እና ትውፊታቸውን በሚያንፀባርቅ መልኩ ደምቀው ይታያሉ።
ይህ ባህላዊ ክዋኔ የማኅበረሰቡ የአንድነት እና የወንድማማችነት እሴት የሚገለጽበት፣ ወጣቶች እና ልጃገረዶች በደስታ የሚያሳልፉበት ልዩ አጋጣሚ ነው።
በአጠቃላይ ይህ ለዘመናት ሳይበረዝ የቆየው የኢራንቡቲ የጥምቀት በዓል፣ እምቅ የቱሪዝም አቅም ያለው ሃብት ነው።

የዘንድሮው የጥምቀት በዓልም በኢራንቡቲ የበለጠ ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት /እህትማማችነት/ እና አንድነትን ባጎለበተ መልኩ በድምቀት ተከብሯል።
እንደ ኢራንቡቲ ያሉ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በሚገባ በማስተዋወቅ እና መሠረተ ልማቶችን በማሟላት፣ ለገጽታ ግንባታ እና ለኢኮኖሚ ዕድገት ይበልጥ መጠቀም ደግሞ ብልህነት ነው። መልካም በዓል!
በጌትነት ተስፋማርያም